አፍሪካ ህብረት፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በመካከላቸው “የተፈጠረውን ውጥረት ከሚያባበስ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ እንዲታቀቡ” አሳሰበ
ህብረቱ የድንበር ግጭቱ በሀገራት ያሉ የውስጥ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ መሆን የለበትም ብሏል
ሙሳ ፋኪ ሁለቱ ወንድማማች ሀገራት በመካከላቸው የተፈጠረው አለመግባበት በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት ከሚያባበስ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ እንዲታቀቡ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተፈጠረውን ወታደራዊ ውጥረት ህብረቱ በቅርበት እየተከታተለው ይገኛል ብለዋል፡፡
በሁለቱም ሀገራት ድንበር ላይ በደረሰው የህይወት መጥፋት አደጋ በእጅጉ ማዘናቸው የገለጹት ሊቀ መንበሩ፤ ሀገራቱ ውጥረቱን ከሚያባብስ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ሙሉ በሙሉ እንዲታቀቡ ተማጽነዋል፡፡
ሁለቱ ወንድማማች ሀገራት በመካከላቸው የተፈጠረው አለመግባበት በውይይት እንዲፈቱት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል ሊቀ መንበሩ።
ሊቀመንበሩ አክለውም የድንበር ግጭቱ፤ በሁለቱ አባል ሀገራት እየተከሰቱ ያሉ የውስጥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎች የመሻት ጥረት የሚያደናቅፍ መሆን የለበትምም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው የቆየ ወንድማማችነት እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል ሀገራት መስራችነታቸው የሚያስቀና ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ የኋላ ታሪካቸው ሁለቱም ወገኖች ለቀጣናዊ መረጋጋት እና የጋራ ጥቅም ሲባል የተከሰተውን ግጭት በአስቸኳይ ለማቆም ያበረታታቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡