የሱዳን ጦር መሪ ሌ/ጀነራል አልቡርሃን ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር እንደሚያስረክቡ ገለጹ
ሌ/ጀነራል አልቡርሃን መቼ ስልጣን ሊያስረክቡ እንደሚችሉ አልገለጹም
የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች ስልጣን እንዲያስረክቡ ህዝቡ አመጹን እንደቀጠለ ነው
የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር እንደሚያስረክቡ ገለጹ፡፡
የሱዳን ጦር ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላህ ሀምዶክን ከስልጣን በማውረድ ሙሉ በሙሉ ስልጣኑን መቆጣጠሩን ተከትሎ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያቶች የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
በሱዳን ከተካሄደው መፈንቅለ መንግስት በኋላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደገባች ይታወሳል።
ቅርቡ ሱዳናውያን ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያስችለናል ያሉትን ንግግር ቢጀምሩም የአፍሪካ ህብረት ግልጸኝነት ይጎድለዋል በሚል ራሱን ከድርድር ሂደቱ ማግለሉ ይታወሳል።
የሱዳናዊያን ተቃውሞ እየበረታ መሄዱን ተከትሎም ሀገሪቱን እየመሩ ያሉት ጀነራል አልቡርሃን ለህዝቡ ባሰሙት ንግግር ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር እንደሚያስረክቡ ገልጸዋል፡፡
ጀነራሉ በንግግራቸው አክለውም የሱዳን ጦር በሀገሪቱ በሚደረገው የዲሞክራሲ ሽግግር ሂደት ውስጥ የራሱን አስተዋጾ ማበርከቱን ገልጸው የሲቪል አስተዳድር እንዲመጣ ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
በቀጣይ በሚደረጉ የፖለቲከኞች ውይይት ላይም ወታደራዊ አመራሩ እንደማይሳተፍ የጠቀሱት ጀነራል አልቡርሃን ስልጣን መቼ ለሲቪል አስተዳድሩ እንደሚመልሱ አልጠቀሱም፡፡
የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግስት በሀገሪቱ የተጀመረውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ በሚል 145 የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር መልቀቁ ይታወሳል፡፡
በሌ/ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ጨምሮ 111 ደርሷል።
የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መረጃ ባሳለፍነው ሳምንት በኦምዱርማን እና በካርቱም ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ዘጠኝ ሰዎች ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመትው መሞታው ተነግሯል።
መንግስታዊ ያልሆነው ይህ የዶክተሮች ኮሚቴ በሰጠው መግለጫው፤ የሱዳንን ወታደራዊ አስተዳድር ለመቃወም ወደ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ደረታቸው እና ጭንቅላት ላይ በጥይት ተመትተው መሞታቸውን አስታውቋል።