በደቡብ ሱዳን በጎሳ ግጭት ምክንያት 56 ሰዎች ተገደሉ
በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ጆንግሌይ ክልል በኑዌር እና ሙርሌ ጎሳ አባላት ለአራት ቀናት የዘለቀ ውጊያ ተደርጓል
የመንግስታቱ ድርጅት ሰላም ማስከበር ተልዕኮም ግጭቱን ለማረጋጋት እየሰራሁ ነው ብሏል
በደቡብ ሱዳን በጎሳ ግጭት የ56 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ጆንግሌይ ክልል በኑዌር እና ሙርሌ ጎሳ አባላት ለአራት ቀናት የዘለቀ ውጊያ መደረጉንም ነው ሬውተርስ የአይን አማኞችን ዋቢ አድርጎ ያስነበበው።
የታጠቁ የኑዌር ጎሳ አባላት ወጣቶች በሙርሌዎች ላይ በመተኮስ ግጭቱን ማስጀመራቸው ተነግሯል።
ጉምሩክ እና ሊኳንጎሌ በተባሉት ወረዳዎች ከአራት ቀናት በፊት የጀመረው ግጭት እስካሁን አልበረደም ነው ያሉት አብርሃም ኬላንግ የተባሉ የመንግስት የስራ ሃላፊ።
መንግስት ግጭቱን ለማብረድ እና ለተጎዱት ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረግ ስለመሆኑም ነው ያነሱት።
በግጭቱ ህይወታቸው ካለፈው 56 ሰዎች ውስጥ 51ዱ ጥቃቱን ያስጀመሩት የኑዌር ጎሳ አባላት ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።
በደቡብ ሱዳን የመንግስታቱ ድርጅት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ባለፈው ሳምንት የታጠቁ የኑዌር ጎሳ አባላት ወጣቶች በሙርሌዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
ይሁን እንጂ በ2011 ነጻነቷን ያወጀችው ሀገር ግጭቱን ማስቆም አልቻለችም።
የሰላም ማስከበር ተልዕኮው የተከሰተውን የጎሳ ግጭት ለማብረድ በተሽከርካሪዎች የሚያደርገውን ቅኝት ማጠናከሩን ገልጿል።
ደቡብ ሱዳን በተለይ ኑሯቸውን በአርብቶ አደርነት ያደረጉ ሰዎች ለከብት እና መሬት በሚያደርጓቸው ውጊያዎች በርካታ ዜጎቿን አጥታለች።