በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰ ግጭት 166 ዜጎች መሞታቸው ተገለጸ
በቅርቡ በጀመረው ግጭት ምክንያት ቢያንስ 3 ሺህ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን ተሰዷል ተብሏል
በግጭቱ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች መፈናቀላቸውንም ተመድ ገልጿል
በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰ ግጭት 166 ዜጎች መሞታቸው ተገለጸ።
በደቡብ ሱዳን የላይኛው ናይል ግዛት በተቀሰቀሰው ግጭት 166 ንጹሀን ዜጎች መሞታቸውን እና ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር አስታወቀ።
የድርጅቱ ሃላፊ ቮልከር ቱርክ በሰጡት መግለጫ “እነዚህ ከስርዓተ ጾታ ጋር የተዛመዱ ጥቃቶች፣ አፈናዎች፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ የተያያዙ ግድያዎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ እና ወንጀሎች ናቸው እናም መቆም አለባቸው” ብለዋል፡፡
የአካባቢው ባለስልጣናት እና የማህበረሰብ መሪዎች ትጥቅ ባነገቡ ቡድኖቹ መካከል ያለውን ውጥረት ማርገብ ካልቻሉ የቅርብ ጊዜው ደም መፋሰስ ከክልሉ አልፎ ይስፋፋል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተናግረዋል ኃላፊው፡፡
"የደቡብ ሱዳን መንግስት በሁከቱ ላይ ፈጣን፣ ጥልቅ እና ገለልተኛ ምርመራ ማካሄድ እና ተጠያቂ የሆኑትን ሁሉ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ተጠያቂ ማድረግ አለበትም" ሲሉም አክለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩኤንኤችሲአር) ግጭቱ በነሀሴ ወር በላይኛው ናይል መንደር ውስጥ ከጀመረው ጦርነት የቀጠለ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ሌሎች የ የጆንግሌይ እና ወደ ሌላሎች ግዛቶችና አካባቢዎች መዛመቱ ገልጿል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የሀይማኖት አባቶችም በተመሳሳይ በተቀናቃኝ ወጣቶች መካከል የተፈጠረው ግጭት ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ ተፈናቃዮች ወዳሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎችም ጭምር መዛመቱን አስጠንቅቀዋል።
በደቡብ ሱዳን አንዳንድ አካባቢዎች በግጦሽ ፣ በውሃ ፣ በእርሻ መሬት እና በሌሎች ሀብቶች ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች ብዙ ጊዜ ወደ ሞት የሚያደርሱ ሁከቶች እንደሚፈጥሩ ይታወቃል።
በቅርቡ በጀመረው ግጭት ምክንያት ቢያንስ 3 ሺህ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሱዳን መሰደዳቸውንም የተመድ መረጃ ያመለክታል፡፡