ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ማዕከል ካፓ (CAPA) ለአቶ ተወልደ ገብረማርያም እውቅና ሰጠ
ካፓ (CAPA-) የተሰኘ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ማእከል ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እውቅና አበርክቶላቸዋል፡፡
”የዓመቱ የአየር መንገዶች ዋና ስራ አስፈጻሚ“ የተሰኘው እውቅና ለአቶ ተወልደ የተሰጣቸው ለአየር መንገዱ እድገት ለተጫወቱት የላቀ የአመራርነት ሚና መሆኑን ማዕከሉ አስታውቋል፡፡ በዚህም ለ አቪዬሽን ኢንዱስትሪው እድገት አቶ ተወልደ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ በማዕከሉ ተመስክሮላቸዋል፡፡
የሽልማት ስነ ስርዓቱ የተካሄደው ትናንት ህዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በማልታ መሆኑን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚያስተናግዳቸው መንገደኞች ቁጥር፣ በገቢ መጠን እና የተለያዩ ዘርፎች ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ቀዳሚ አየር መንገዶች ተርታ የሚሰለፍ ሲሆን ለዚህ ስኬቱም የዋና ስራ አስፈጻሚው የአመራር ብቃት ዋና ምክኒያት እንደሆነ ይታመናል፡፡
እንደአውሮፓውያኑ ከ1966 ጀምሮ የሚታተመው ኒው አፍሪካን ማጋዚን የተሰኘ (New African Magazine) የተሰኘ ወርሀዊ መጽሔትም በዚህ ወር ህትመቱ ከ100 ከፍተኛ የ2011 ተጽእኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን መካከል በቢዝነስ ዘርፍ አቶ ተወልደን መርጧቸዋል፡፡
መጽሐየቱ፣ በርካታ የአፍሪካ አየር መንገዶች በከፍተኛ ኪሳራ እና ቀውስ ውስጥ በሚገኙበት በዚህ ጊዜ በከፍተኛ ትርፋማነት ውጤታማነቱን አስቀጥሎ የሚጓዘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የአየር መንገዱን ስራ አስፈጻሚ የአፍሪካ ኩራቶች መሆናቸውን በመጥቀስ አሞካሽቷቸዋል፡፡