በሳዑዲ ዓረቢያ እስር ላይ የነበሩ 840 ኢትዮጵያውያን ተመለሱ
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት በሳዑዲ እስር ቤቶች ከአምስት እስከ ስምንት አመት ተፈርዶባቸው ይገኙ የነበሩ 840 ኢትዮጵያውያን በፈቃዳቻው በዛሬው ዕለት ህዳር 26 ቀን 2012 ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
ኢትዮጵያውያኑ ቀይ ባህርን አቋርጠው የሳዑዲን ድንበር ሲሻገሩ የተያዙ እና በሳዑዲ ዓረቢያ በጂዳ እና ጂዛን ግዛት በሚገኙ እስር ቤቶች የሚኖሩ ናቸው።
ተመላሾቹ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ዮሃንስ ሾዴ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ተመላሾቹ በአዲስ አበባ በሚገኘው በአለም አቀፍ የፍልሰተኞች የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ እንደተደረገላቸውም ተገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ሀገር በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መብታቸው ተከብሮ በፈቃዳቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኝ መግለጹን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡
ምንጭ፡-ኤፍቢሲ