ወደ ትግራይ ክልል በሚጓጓዙ ነገሮች ላይ የተጣሉ ጥብቅ ፍተሻዎች እንዲላሉ የአውሮፓ ህብረት ጠየቀ
የአውሮፓ ህብረት ለትግራይ አድልቷል በሚል የሚነሱ ጥያቄዎችንም አስተባብሏል
ትግራይ ክልል ባንክ እና ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ህብረቱ አሳስቧል
ወደ ትግራይ ክልል በሚጓጓዙ ነገሮች ላይ የተጣሉ ጥብቅ ፍተሻዎች እንዲላሉ የአውሮፓ ህብረት ጠየቀ፡፡
የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች በኢትዮጵያ የሑለት ቀናት ጉብኝት አድርገው ትናንት ወደ ብራስልስ ተመልሰዋል፡፡
ኮሚሽነር ዣኔዝ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ ትግራይ ክልልን እና ሶማሊ ክልልን የጎበኙ ሲሆን በአዲስ አበባም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርት እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ወደ ብራስልስ ከመመለሳቸው በፊት በአዲስ አበባ ባለው የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ቢሮ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ኮሚሽነር ዣኔዝ ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ባዩት ነገር ማዘናቸውን እና በድርቁ ምክንያትም በሶማሊ ክልል የተጎዱ ሴቶች እና ህጻናትን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በመቀሌ ቆይታቸው ከደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር መወያየታቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ አይደር ሆስፒታልን እና ተፈናቃዮችን እንደጎበኙ ተናግረዋል፡፡
ጉብኝታቸውም ወደ ትግራይ ክልል እየገባ ያለው ነዳጅ፣ጥሬ ገንዘብ፣ ምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ቁሳቁሶች አነስተኛ መሆናቸውን እንዳዩ ለጋዜጠኞቹ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ይሄን ያክል ዋጋ ሊከፍሉ እንደማይገባ እና ጦርነቱ ብዙ ጉዳቶችን እንዳደረሰ የተናገሩት ኮሚሽነር ዣኔዝ ጉዳቱ ጥልቅ መሆኑን አክለዋል፡፡
ሰራተኞች ደመወዝ ከተቀበሉ ከአመት በላይ እንዳለፋቸው፣ ዓለም አቀፍ የረድዔት ተቋማት ለሰራተኞቻቸው በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ደመወዝ መክፈል እንዳልቻሉ ማስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ህዝብ ይህ ሁሉ ጉዳት እንዳለ ሆኖ ከዓለም ተነጥሎ ሊኖር አይገባም የፌደራል መንግስት ባንክ፣ቴሌኮም እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ወደ አገልግሎት ሊያስገባ ይገባልም ብለዋል፡፡
ወደ ክልሉ በሚገቡ የተለያዩ አስፈላጊ ቁሳቁሶች እና ምርቶች ላይ ጥብቅ ፍተሻ መደረጉ በሚፈለገው ፍጥነት ወደ ክልሉ በሚገቡ ነገሮች ላይ እጥረት እንዲከሰት ማድረጉንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን አማራ እና አፋር ክልሎችም ተጎጂ ናቸው፣ የሁንና ህበረቱ ትኩረት እየሰጠ ያለው ለትግራይ ክልል ብቻ ነው፡፡ ይሄንን ተከትሎም የአውሮፓ ህበረት ገለልተኛ አይደለም በሚል ጥያቄ ይነሳበታል እና ለዚህ ምላሻችሁ ምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም
“የአውሮፓ ህብረት ውግንናው ለሰብዓዊ መብት መከበር ብቻ ነው፣ ጦርነቱ አፋርን እና አማራ ክልሎችን እንደጎዳም እናውቃለን፣ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረግን ነው፣ በቀጣይ በሚኖረኝ የኢትዮጵያ ጉብኝትም ሁለቱን ክልሎች እጎበኛለሁ፣ የሚነሳብን የገለልተኝነት ጥያቄም ፍጹም ትክክል አይደለም“ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡