አሜሪካ፤ በኦሮሚያ ክልል የተገደሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ጉዳይ እንደሚያሳስባት ገለጸች
ግድያውን የኮነነው ኢሰመኮ በአካባቢው አሁንም ሰጋት አለ ሲል ገልጿል
አሜሪካ ፍትህ እንዲሰፍንና ተጠያቂነት ያለበት ብሔራዊ ዕርቅ እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች
አሜሪካ በኦሮሚያ ክልል የተገደሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ጉዳይ እንደሚያሳስባት አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በምዕራብ ወለጋ በተገደሉ ንጹሃን የአማራ ብሔር ተወላጆች ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በጥቃቱ ህይወታቸው ላለፈ ዜጎች ሀዘኑን የገለጸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኢትዮጵያውያን ችግሮችን ለማስወገድ ከግጭት ይልቅ ሰላማዊ ንግግርን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም ነው ዋሸንግተን ያሳሰበችው፡፡
ሁሉንም ያሳተፈ፤ ለሁሉም ተጎጂዎች የሚሆን ፍትህና ተጠያቂነት ያለበት ብሔራዊ ዕርቅ እንዲደረግም ነው አሜሪካ ጥሪ ያደረገችው።
አሜሪካ እንደዚህ አይነት ግጭቶች የሚቆሙበት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲመጣም ጠይቃለች፡፡
ከአሜሪካ በተጨማሪም የኢራን መንግስት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በተገደሉ ዜጎች ዙሪያ ሃዘኑን ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ንጹሃን በተጨፈጨፉበት አካባቢ የመከላከያ ሰራዊት ተሰማርቶ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱን የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)ም አውግዘዉታል፤አጥፊዎችም እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ከትናንት በስትያ ባወጣው መግለጫ በመንግስት እና በሽብር በተፈረጀው ሸኔ ቡድን መካከል ከተካሄደው ውጊያ ጋር በተያያዘ፣ ታጣቂ ቡድኑ በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን መግለጹ ይታወሳል።
ኢሰመኮ የአካባቢዉ ነዋሪዎች አሁንም የደህንነት ሰጋት እንዳለባቸው እና ድጋፍ እየጠየቁ መሆናቸውንም በመግለጫው ጠቅሶ ነበር።