የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በስምምነት ተቋጨ
የአውሮፓ ሕብረት ከኮሮና ለማገገም በድጋፍ እና በብድር ለአባል ሀገራት የሚሰጥ750 ቢ/ዩሮ አጸደቁ
ሕብረቱ ለቀጣይ ሰባት ዓመታት በጀት እና ለኮሮና ማገገሚያ 1.82 ትሪሊዮን ዩሮ በጀት አጽድቋል
ሕብረቱ ለቀጣይ ሰባት ዓመታት በጀት እና ለኮሮና ማገገሚያ 1.82 ትሪሊዮን ዩሮ በጀት አጽድቋል
የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት መሪዎች ባደረጉት ስብሰባ ኮሮናን ለመከላል የሚያግዝና ለቀጣይ ሰባት ዓመታት የሚሆን በጀትን አጽድቀዋል፡፡ መሪዎቹ ከአርብ ጀምሮ ለስብሰባ ቢቀመጡም እስከ 11ኛው ሰዓት ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም ነበር፡፡ ዩሮ ኒውስ በዘገባው “አሁን ላይ መሪዎቹ የደረሱት ስምምነት አውሮፓ ጠንካራ መሆኗን ያመለክታል” ብሏል፡፡
መሪዎቹ ከኮሮና ቫይረስ በኋላ ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ መከላከል የሚያስችል በጀት ከመመደብ አልፎም በብዙ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የሕብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡዙላ ቮን ደር ላየን አስታውቀዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በአውሮፓ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ቀውስን ሲያስከትል የአውሮፓ ሕብረት ፈጥኖ አልደረሰም በሚል ሲተች ቢቆይም አሁን ግን ሰፊ ውይይት ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ትናንት ከሰዓት የቀጠለው ይህ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስተላለፉን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በዚህም ከኮሮና ቫረስ ወረርሽኝ ጉዳት ለማገገሚያ የሚሆን 750 ቢሊዮን ዩሮ ያጸደቀ ሲሆን ይህም በብድርና በሥጦታ ለአባል ሀገራቱ እንደሚዳረስ ነው ሥምምነት ላይ የተደረሰው፡፡ በኮሮና ቫረስ እጅጉን በተጎዱና ገንዘብ ቆጣቢ በሚባሉት አባል ሀገራት መካከል ከረር ያለ ክርክርና መከፋፈል እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
360 ቢሊዮን ዩሮ የሚሆን ገንዘብ ለአባል ሀገራቱ በብድር እንዲሰጥ የተወሰነ ሲሆን የዚህ ወለድም አነስተኛ ይሆናል ነው የተባለው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰባቸው ሀገራት ደግሞ 390 ቢሊዮን ዩሮ እንዲሰጣቸው የተወሰነ ሲሆን ጣሊያንና ስፔን ደግሞ ዋነኛ ተቀባዮች እንደሚሆኑ ነው የዩሮ ኒውስና ቢቢሲ ዘገባ የሚመለክተው፡፡
ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ ለተጎዱ ሀገራት 500 ቢሊዮን ዩሮ በድጋፍ መልክ እንዲሰጥ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በገንዘብ ላይ ጠንካራ አቋም እንዳላቸው የሚገልጹት ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ኦስትሪያ፣ ኔዘርላንድስ እና ፊንላንድ በስጦታ የሚሰጠው ገንዘብ ከ 375 ቢሊዮን ዩሮ መብለጥ የለበትም በሚል ተቃውመዋል፡፡ ጣልያንና ስፔን ደግሞ ከ400 መቶ ቢሊዮን ዩሮ ማነስ የለበትም የሚል ክርክር ቢያነሱም በስተመጨረሻ ከ750 ቢሊዮኑ 390ው በስጦታ እንዲበረከት ከስምምነት ተደርሷል፡፡
ህብረቱ ለቀጣይ ሰባት ዓመታት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዩሮ በላይ በጀትም አጽድቋል፡፡ በዚህም መሰረት ባጠቃላይ 1 ነጥብ 82 ትሪሊዮን ዩሮ ለኮሮና ማገገሚያና ለሰባት ዓመት የሚሆን በጀት በህብረቱ ጸድቋል፡፡ ይህ የአባል ሀገራቱ ስብሰባ የተካረረ ውይይት የነበረበት ቢሆንም ለአውሮፓ ግን ታሪካዊ ነው አስብሏል፡፡ የሕብረቱ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሸል ስምምነቱ የህብረቱን ጥንካሬ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “ይህ ዕለት ለአውሮፓ ታሪካዊ ነው” ሲሉ የቤልጀም ጠቅላይ ሚኒስትር ሶፊ ዊሊምስ “አውሮፓ በወደፊት ዕጣው ላይ እንዳሁኑ አስቦና ተግብሮ አያውቅም” በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
የሕብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡዙላ ቮን ደር ላየን በበኩላቸው “አሁን ታሪካዊ እርምጃ ወስደናል ፤ በዚህም መኩራት አለብን፡፡ ነገር ግን አሁንም በጣም ጠቃሚ እርምጃዎችን መውሰድ ይቀረናል” ብለዋል፡፡ የኔዘርላድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ ስምምነቱ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው “በውይይቱ የነበሩ ልዩነቶችንም ዕውቅና ልንሰጣቸው ይገባል ተፈጥሯዊ ናቸውና” ብለዋል፡፡
አርብ ዕለት የተጀመረው ይህ ስብሰባ ለ 90 ሰዓት ያህል ንግግር የተደረገበትና በአውሮፓውያኑ 2000 በፈረንሳይ ኒስ ከተማ ከተደረገው ስብሰባ በኋላ ረጅሙ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡