ኮሮና ጣሊያን ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ምክንያት ይሆናት ይሆን?
በፈረንጆቹ ጥር 2020 ዩናይትድ ኪንግደም ከህብረቱ ስትወጣ የህብረቱ አባል ሀገራት ቁጥር ከ28 ወደ 27 ዝቅ ብሏል
በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ የተጎዳቸው ጣሊያን በችግሬ ጊዜ የአውሮፓ ህብረት አልደረሰልኝም ስትል ጠንካራ ወቀሳ አቅርባ ነበር
በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ የተጎዳቸው ጣሊያን በችግሬ ጊዜ የአውሮፓ ህብረት አልደረሰልኝም ስትል ጠንካራ ወቀሳ አቅርባ ነበር
ጣሊያን አሁን ላይ ከ233 ሺ በላይ ዜጎቿ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን 33 ሺ 530 የሚሆኑት ደግሞ ለህልፈት ህይወት ተዳርገውባታል፡፡ በአውሮፓ በወረርሽኙ ብዙ ሕዝብ የሞተባት ጣሊያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቿ ተገድበው ዜጎቿም ለከፍተኛ ችግር ተዳርገውባታል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በጣሊያን በየዕለቱ ብዙዎችን ሲቀጥፍ ሀገሪቱ አባል የሆነችበት የአውሮፓ ሕብረት “ዝምታን መርጦ ነበር”በሚል የሀገሬው ሰዎች እየዘመቱበት ነው፡፡የጣሊያን መንግስትና ዜጎች በቸገራቸው ጊዜ የብራሰልሱ ተቋም “አይዟችሁ” የሚል የሥነ ልቦና ጥገና እንኳን አለማድረጉ እንዳስቆጣቸው ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡
ጉዳዩን በቁጣ ብቻ ማለፍ ያልፈለጉት ጣሊያናውያን “በክፉ ቀን ያልደረሰልን ሕብረት መቼ ሊጠቅመን ነው “በሚል ንቅናቄ መጀመራቸውም ተሰምቷል፡፡ በዚህም ጣሊናውያን የብሪታኒያን መንገድ ለመከተልና ከብራሰልስ አባልነት ለመውጣት ስለመፈለጋቸው እየተገለጸ ነው ፡፡
አሁን የሮም ሰዎች ከአውሮፓ ህብረት ለመነጠል ማሰብ ብቻ ሳይሆን በራሳቸው እየወሰኑም ነው ተብሏል፡፡ ምንም እንኳን ከኮሮና በፊት ከህብረቱ ለመነጠል ሃሳብ አቅርበው የነበሩ ጣሊናውያን ቢኖሩም ቁጥራቸው ግን እምብዛም እንዳልነበረ ሲገለጽ ነበር፡፡ እንዳውም እ.ኤ.አ በ2018 29 በመቶ የሚሆኑት ጣሊናውያን ከአውሮፓ ሕብረት ለመውጣት ፍላጎት እንዳላቸው ሲገለጽ የቆየ ቢሆንም አሁን ግን ቁጥሩ እየጨመረ መሆኑን ተንታኞች እየተናገሩ ነው፡፡
በሚያዚያ በተሰራ ጊዜያዊ መጠይቅ 59 በመቶ የሚሆኑት የመጠይቁ መላሾች “የአውሮፓ ሕብረት ትርጉም አልባ ተቋም ነው“ የሚል ምላሽ ስለመስጠታቸው ተዘግቧል፡፡ እነዚሁ የመጠይቁ መላሾች “ሩሲያና ቻይና ግን የቁርጥ ቀን ወዳጆቻችን ናቸው“ ሲሉ ከመላሾቹ ምናልባትም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጀርመንን እንደ ጠላት ያያሉም ተብሏል፡፡
ቴርሞ ሜትሮ ፋዉንድ የተባለ ድርጅት በሰራው ጥናት ደግሞ 40 በመቶ ጣሊያናውያን ሀገራቸው ከህብረቱ እንዲትወጣ የሚደግፉ ስለመሆናቸው አረጋግጧል፡፡ 40 ነጥብ 9 የሚሆኑት ግን ጣሊያን በህብረቱ መቆየት እንደሚሻላት መክረዋል ብሏል አጥኝው ተቋም፡፡ ይህ ቁጥር ያሻቀበውና እንደ አዲስ ጥያቄ የተነሳው ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ ወረርሽኙ ከዚህ የባሰ የፖለቲካ ቀውስ እየፈጠረ ስለመሆኑም ተነስቷል፡፡
በአውሮፓ ሦስተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ጣሊያን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚዋ እስከ 9 በመቶ በሚደርስ ጉዳት ሊጠቃ እንደሚችል ይገመታል፡፡ አሁን አስፈላጊ ከሆነ አውሮፓ ህብረትን ተሰናብተነው “ከህብረቱ እንወጣለን“ የሚሉ ጣሊያናውያ ቁጥር ስለመጨመሩ ብዙ የፖለቲካ ሰዎችና መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ናቸው፡፡
የአውሮፓ ሕብረት በጣሊያን ችግር ጊዜ ከጎኗ ባለመሆኑ ሚያዚያ ላይ በኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮንደር ሌየን በኩል ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋበት ጊዜ ቻይናና ሩሲያ ወታደራዊ የህክምና ሰዎችንንና ከቫይረሱ መከላከያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ለጣሊያን መላካቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን ማድረግ ያለበት የአውሮፓ ሕብረት ሆኖ ሳለ ቤጅንግ እና ሞስኮ ይህንን በማድረጋቸው ጣሊናውያን ከብራሰልስ ይልቅ ለእነርሱ ልዩ ስሜት እንዳላቸው እየተናገሩ ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት የጣሊያን መንግስትና ዜጎች አሁን ላይ ስለህብረቱ በጎነት ማውራት እና መስማት እንደማይፈልጉ እየገለጹ ነው፡፡ በፈረንጆቹ ግንቦት 27፣ 2020 ፖለቲካል ሙቭመንት ኢታሊያ ሊበራ የተባለው ፓርቲ ጣሊያን ከአውሮፓ ሕብረት እንድትወጣ የሚጠይቅ ሰነድ ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማስገባቱን አስታውቋል፡፡ፓርቲው ጣሊያን ከህብረቱ እንድትወጣ ፊርማ ማሰባሰቡንም ጭምር ገልጿል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት ብዙ በጎ ነገሮች እንዳሉት የሚናገሩት የዚህ ፓርቲ ሰዎችና ሌሎች ዜጎች አሁን ግን ብንወጣ ይሻላል ባይ ናቸው፡፡ ነጻ የሰዎች እንቅስቃሴ እና ወንጀለኞችን በህብረት የመያዝ ስራዎች ሕብረቱ ከሚከውናቸው መልካም ስራዎች መካከል ናቸው የሚሉት ዜጎቹ እነዚህን የባለብዙ ወገን ስራዎች ግን ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ውጭ መስራት እንደሚቻል ያነሳሉ፡፡
ቢቢሲ ከ2 ሳምንታት በፊት በተሰራ መጠይቅ 42 የመጠይቁ መላሾች 42 በመቶ የሚሆኑት ሀገራቸው ከህብረቱ እንዲትወጣ እንደሚፈልጉ ዘግቦ ነበር፡፡ አሁንም ይህ ነገር ተባብሶ ጣሊያናውያንም ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ግፊት እያደረጉ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ይሁንና ከዚሁ መጠይቅ መላሾች መካል ሩብ ያህሉ የአውሮፓ ህብረት በተጎዳችው ጣሊያን ላይ ተጨባጭ እርምጃ የሚወስድና የሚታደጋት ከሆነ በህብረቱ ብትቆይ ምርጫቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ይህ የኮሮና ወረርሽኝ በአውሮፓ የወደፊት ዕጣ ላይ ስጋት ስለመደቀኑ ለቢቢሲ መናገራቸውም ተሰምቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1958 ቤልጄም፣ ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ጣሊያን፣ሉክዘምበርግ እና ኔዘርላንድስ የአውሮፓ ኢኮኖሚክ ኮሚኒቲ የሚባል የኢኮኖሚ ትብብር የመሰረቱ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1993 የአውሮፓ ህብረት የሚል ስያሜ ቀየረ፡፡ በጥር 2020 ደግሞ 28 ከነበሩት አባሎቹ መካከል ዩናይትድ ኪንግደም ተቀንሳ አባል ሀገራቱ 27 ሆነዋል፡፡
አሁን ደግሞ ለህብረቱ ከፍተኛ ገንዘብ ከሚያዋጡ ሀገራት አንዷ ጣሊያን ከህብረቱ ስለመውጣት እያሰበች ይመስላል፡፡