የአውሮፓ ህብረት በመራዊ ከተማ ንጹሃን የተገደሉበት ጥቃት በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ጠየቀ
ህብረቱ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙ የዜጎችን ሰብአዊ መብት በእጅጉ ይገድባል ብሏል
ኢሰመኮ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ በመራዊ ከተማ በርካታ ንጹሃን በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል
የአውሮፓ ህብረት በመራዊ ከተማ ንጹሃን የተገደሉበት ጥቃት በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ጠየቀ።
የህብረቱ ቃል አቀባይ ባወጣው መግለጫ በከተማዋ ንጹሃን ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች መፈጸማቸው እንዳሳሰበው ገልጿል።
በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዳግም መራዘሙ የዜጎችን የሰብአዊ መብት በእጅጉ የሚገድብ መሆኑም አሳሳቢ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
የአውሮፓ ህብረት የመራዊው ግድያ በገለልተኛ ተቋም እንዲጣራ የጠየቀበትን መግለጫ ከማውጣቱ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በመራዊ ከተማ ስለነበረው ግጭትና የንጹሃን ሞት ዝርዝር መግለጫ አውጥቷል።
ኢሰመኮ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ቢያንስ 45 ንጹሃንን መግደላቸውንና የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የሚያመላክት መግለጫ ነው ያወጣው።
“የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በሸበል በረንታ እና ቋሪት ወረዳዎችም ከ21 በላይ ሲቪሎች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ከምስክሮች አረጋግጫለሁ ያለው ኮሚሽኑ በግጭት ውስጥ ያሉ ሁለቱም ወገኖች ለሰላማዊ ንግግር ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጠይቋል።
የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫም በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለሚደረጉ የሰላም ንግግሮች ድጋፍ አልማድረግ ዝግጁ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
“ኢትዮጵያውያን በመላው የሀገሪቱ ክፍል የሚታዩ ግጭቶች በዘላቂነት ሊቆሙ የሚችሉት በሰላማዊ ንግግርና እርቅ ብቻ መሆኑን በመረዳት ለመመካከር ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል”ም ብሏል።
ባለፈው ሳምንት በህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የታጠቁ ሃይሎች ነፍጣቸውን ካስቀመጡ ለመነጋገር ዝግጁ ነን ማለታቸው ይታወሳል።