ወደ መደበኛ ኃይል አልገባም ብሎ የአመፅ መንገድን የመረጠውን የፋኖ ኃይል "በመረጠው መንገድ መስመር አስይዘነዋል"- ጄኔራል አበባው ታደሰ
ለፋኖ 'ልዩ ኃይል' የተሰጠው አማራጭ እንደተሰጠውየጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር አስታውቀዋል
ጄኔራል አበባው ታደሰ ፋኖን ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት መንግስት እቁዱን እንዳሳካ ተናግረዋል
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ መከታ ከተባለ የመከላከያ ሰራዊት መጽሄት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከፋኖ ጋር ያለውን ግጭት በተመለከተ ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ለፋኖ የልዩ ኃይል አማራጭ እንደተሰጠው መግለጻቸውንም ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በዚህም "ፖሊስ የሚሆን ፖሊስ፤ መከላከያ የሚሆን መከላከያ ይግባ ብለን ክፍት አድርገንለታል" በማለት ተናግረዋል።
የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት ጄኔራሉ፤ የመንግስትን ፕሮግራም አልቀበልም ያሉና የኃይል አማራጭ የተከተሉትን የፋኖ ኃይሎች በሁለት መንገድ አስተናግደናል ብለዋል።
ፕሮግራሙን ለማስረዳትና ለማወያየት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል ያሉ ሲሆን፤ "አብዛኛው ሊባል የሚችለው ወደ ተፈለገው መስመር ገብቷል" በማለት ተናግረዋል።
"አሻፈረኝ ብሎ የአመጽ መንገድን የመረጠውን ግን ህጋዊው አሰራር የግድ ተግባራዊ መደረግ ስለነበረበት በመረጠው መንገድ ሄደን መስመር አስይዘነዋል" ብለዋል።
አጠቃላይ ሲታይ መንግስት እቅዱን እንዳሳካ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ተናግረዋል።
- በአማራ ክልል መከላከያ ሰራዊትና ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
- “ሠራዊቱ የምዕራፍ አንዱን ጦርነት አጠናቅቆ ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ ነው”-ጄ/ል አበባው ታደሰ
ጄኔራል አበባው ታደሰ ከልዩ ኃይል ጋር በተያያዘም አሁን ላይ “ምንም በልዩ ሃይል የሚታዘዝ አደረጃጀትና የኮማንድ ስርዓት ያለው አሁን የለም፤ እንደ ሃይል ወይ መከላከያ ሆኗል ወደ መደበኛ ፖሊስ ሆኗል ወይም ደግሞ ፌዴራል ፖሊስ ሆኗል። ይሄ በተሳካ መንገድ ነው የተፈፀመው” ብለዋል።
በልዩ ሃይል እና በኢ መደበኛ አደረጃጀትና ቅርፅ ተደራጅተው ሲሠሩ የነበሩት ሐይሎች አሁን ወደ ፌዴራልና ክልል ፖሊስ ወደ መከላከያ ሲመጡ ሀገራዊ ተልዕኮ መቀበል እንዲችሉ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የትግራይ ኃይልን በተመለከተ ከትግራይ ጋር ተያይዞ ያለውም እንደ ማንኛውም ክልል እሱም የሚኖረው መደበኛ ፖሊስ እና ሚሊሻ ብቻ ፤ በተቀመጠለት ስታንዳርድ ብቻ ነው የሚሄደው ሲሉም ምክትል እታማዦር ሹሙ ተግናረዋል።
ሀገራዊ ወታደራዊ አቅምን ለማጠናከር የጸጥታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አደረጃጀቶችን ወደ ህጋዊነት የማስገባት አሰራርን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።
የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎች ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ባሉት አማራጮች ብቻ ችግሮችን እንዲፈቱ የሚያስችል እድል ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን በህዝብ ምርጫ ብቻ መያዝ እንዲቻል ያደርጋል ብለዋል።