ፖለቲካ
የአውሮፓ ህብረት በስርቆት ምክንያት በሶማሊያ ይሰጥ የነበረውን የምግብ እርዳታ አቋረጠ
የአውሮፓ ህብረት ለሶማሊያ የድርቅ ተጎጂዎች ባለፈው ዓመት ሰባት ሚለዮን ዶላር መለገሱ ተነግሯል
ህብረቱ ለብልሹ አሰራር ግን ትዕግስት የለኝም ብሏል
የአውሮፓ ህብረት በሶማሊያ ለዓለም የምግብ ፕሮግራም ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ በጊዜያዊ ማቋረጡን አስታውቋል።
ህብረቱ የመንግስታቱ ድርጅት በሶማሊያ ለድርቅ ተጎጂዎች የተመደበ የምግብ እርዳታ ለሌላ አላማ መዋሉንና መሰረቁን ካሳወቀ በኋላ ነው እርምጃውን የወሰደው።
ባለፈው ዓመት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ከሰባት ሚለዮን ዶላር በላይ መለገሱን ሮይተርስ ዘግቧል። ይህም ህብረቱ ለመስጠት ቃል ከገባው ሽራፊው ነው ተብሏል።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትም በሁለትዮሽ ስምምነቶች ከዚህ የበለጠ ገንዘብ መስጠታቸው ተነግሯል።
የህብረቱ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሁኔታውን በቅርበት እንደሚከታተሉት ገልጸው፤ ለብልሹ አሰራር ግን ትዕግስት የለንም ብለዋል።
ሮይተርስ ስለ ጉዳዩ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል።
አንድ የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣን እርምጃው ተመድ ምርመራ አከናውኖ ለተጎጂዎች የተመደበውን እርዳታ የሰብዓዊ ሠራተኞች፣ የጸጥታ ኃይሎችና ሹማምንቶች መዝብረውት ተገኝቷል ብለዋል።
ህብረቱ የደህንነት ስርዓት ማስተካከያዎች ከተደረጉ እርዳታውን እንደሚመስል ተነግሯል።