ኢትዮጵያ አልሸባብን ለመዋጋት ተጨማሪ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ልትልክ ነው ተባለ
የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በቅርቡ በአልሸባብ ላይ ስለሚወሰደው ቀጣይ እርምጃ በሞቃዲሾ መምከራቸው አይዘነጋም
ወታደሮቹ በስምንት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሶማሊያ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አልሸባብን ለመዋጋት ተጨማሪ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ሊልኩ መሆኑን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሁሴን ሼክ አሊ አስታወቁ።
ሁሴን ሼክ አሊ ከቪኦኤ የሶማሊያ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ተጨማሪ ወታደሮች የሚልኩት ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ጁቡቲ እና ኬንያ ናቸው፡፡
ይሁን እንጅ አዲሶቹ ወታደሮች በሶማሊያ የአፍሪካ የሽግግር ተልዕኮ ወይም ኤቲኤምኤስ አካል እንደማይሆኑም ተናግረዋል።
“ሀገራቱ በስምንት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሶማሊያ የመግባት እቅድ አላቸው” ያሉት የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ሁሴን ሼክ አሊ፤ ወደ ሶማሊያ ይገባሉ ስለተባሉት ወታደሮች ቁጥር ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡
"የእነሱ (የወታደሮቹ) ሚና በሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎች ትዕዛዝ መሰረት አልሸባብን ለመዋጋት በጋራ ማቀድ እና በጋራ መስራት ይሆናል"ም ብለዋል።
የሶስቱ ሀገራት መሪዎች የካቲት 1ቀን 2023 በአሸባሪው ቡድን አልሸባብ ላይ ስለስለሚወሰደው ቀጣይ የተቀናጀ ወታደራዊ እርማጃ መምከራቸው አይዘነጋም፡፡
መሪዎቹ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፣ አልሸባብን “ለማጥፋት” የተጠናከረ የጋራ ዘመቻ ለማካሄድ ተስማምተናል ብለው ነበር፡፡
ከሶማሊያ በዘለለ የቀጠናው ስጋት መሆኑ የሚነገርለት አልሸባብ በተለይም አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ በትረ ስልጣን ከጨበጡ በኋላ ከሶማሊያ ጦር ከፍተኛ ጥቃት እየተሰነዘረበት እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ነሃሴ 2022 በቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር በአልሸባብ ላይ “አጠቃላይ ጦርነት” ለማካሄድ ማቀዳቸው ተናግረው ነበር፡፡
በዚህም የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ከሃምሌ ወር ጀምሮ በወሰደው መጠነ ሰፊ የማጥቃት እርምጃ አልሸባብ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ አልሸባብ ከዋና ዋና ወታደራዊ ይዞታዎቹ እያፈገፈገ ነውም ተብሏል።