ሶማሊያ እና ኩባ ለ46 አመታት የተቋረጠውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አደሱ
ኩባ በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ወታደሮቿን ለኢትዮጵያ ከላከች በኋላ የሞቃዲሾና ሃቫና ግንኙነት መቋረጡ ይታወሳል
ለአራት አስርት አመታት የተቋረጠው ግንኙነት ኩባ አምባሳደሯን ወደ ሶማሊያ በመላክ ዳግም ተጀምሯል
ሶማሊያ እና ኩባ ከ46 አመታት በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ዳግም ጀምረዋል።
በሶማሊያ የኩባ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ዩዋን ማኑዌል ሮድሪጌዝም የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህ ሞሃመድ አቅርበዋል።
የኬንያ አምባሳደርነትን ደርበው የሚይዙት ሮድሪጌዝ በሞቃዲሾ ቢሮ ባይኖራቸውም ለአራት አስርት አመታት ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት ለማደስ እንደሚሰሩ ነው የሚጠበቀው።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ጃሜህም አዲሱ አምባሳደር የሞቃዲሾ እና ሃቫናን ግንኙነት ለማስተካከል ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ሶማሊያ እና ኩባ በፈረንጆቹ 1972 በይፋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ጀምረዋል።
ከአምስት አመት በኋላ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ግን ሃቫና ለኢትዮጵያ ወታደሮቿን መላኳ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያወሳሉ።
የያኔው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ ከሶቪየቶች ጋር በመሆን ለኢትዮጵያው መንግስቱ ሃይለማርያም ያሳዩት ድጋፍ የዚያድ ባሬን መንግስት ማስቆጣቱ ይታወሳል።
አሁን ከኢትዮጵያም ሆነ ከሩሲያ ጋር መልካም ግንኙነት አለን ያሉት የቀድሞው የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ኢሳ አዋድ፥ የ1977ቱ (የ1969) ጦርነት ዶሴ የተዘጋ ነው፤ ስለቀጣይ ትብብር ማሰብ ይገባል ማለታቸውን የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ኩባ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን ተከትሎ ሃቫና ቀድማ የምታነሳው ጥያቄ በ2019 በሰሜናዊ ኬንያ በአልሸባብ ተጠልፈው በሶማሊያ ስለሚገኙ ሁለት የህክምና ባለሙያ ዜጎቿ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኩባውያኑ ዶክተሮች የት እንደሚሰሩ ባይገለጽም በሶማሊያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ እየሰሩ መሆኑን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
በህክምና ዘርፍ የካበት ልምድ ያላት ኩባ በቀጣይ ከሶማሊያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ተገልጿል።