አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የታገዱ የሩሲያ ንብረቶችን ለዩክሬን ሊሰጡ እንደሚችሉ ጠቆሙ
ስዘርላንድ ከዚህ በፊት የሩሲያዊያንን ሀብት አሳልፋ ለሌላ ወገን እንደማትሰጥ ገልጻለች
ሩሲያ በበኩሏ ድርጊቱ የዓለም አቀፍ ህጎችን ከመጣሱ ባለፈ ሌላ መዘዝ ያስከትላል ማለቷ ይታወሳል
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የታገዱ የሩሲያ ንብረቶችን ለዩክሬን ሊሰጡ እንደሚችሉ ጠቆሙ፡፡
ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው አንድ ወር ብቻ ቀርቶታል፡፡
ይህ ጦርነት በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች እንዲጣሉባት ከማድረጉ ባለፈ ለዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መናርም ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡
አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ሀገራት ከማዕቀቡ ባለፈ የሩሲያ መንግስት እና ባለሀብቶች ንብረት የሖኑ ሁሉንም ሀብቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያገዱ ሲሆን ጦርነቱ መቀጠሉን ተከትሎ ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት የሩሲያዊያንን ገንዘብ ለማዋል ማቀዳቸው ተገልጿል፡፡
በተለይም የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ የታገዱ የሩሲያዊያን መንግስት እና ዜጎች ሀብትን ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እንዲውል እያሰቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር የሆኑት አንድሪው አዳምስ እንዳሉት የታገዱ የሩሲያ መንግስት እና ባለሀብቶች ገንዘቦችን ለዩክሬን የመልሶ ግንባታ ለማዋል ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር ከቀናት በፊት እንዳስታወቀው ሩሲያ በዩክሬን ዋና ዋና መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እያደረሰች ነው፤ የተያዘባት ገንዘብን ዩክሬንን መልሰን ለመገንባት እናውለዋልን፣ ለዚያ የሚያበቃንን ህግ እያዘጋጀንም ነው ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ሩሲያ በበኩሏ በአውሮፓ እና አሜሪካ እንዳይንቀሳቀሱ እገድ የተላለፈባቸው የሩሲያዊያን ሀብትን ለዩክሬን መስጠት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ህግ እንደሌለ ገልጻ ድርጊቱ ሌላ ዓለም አቀፍ መዘዝ ያስከትላል ስትል በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃለች፡፡
የስዘርላንድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኢጋንሲዮ ካሲስ በበኩላቸው ሀገራቸው በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ላይ ገለልተኛ መሆኗን ተናግረው የሩሲያ መንግስት እና ሩሲያዊያን ባለሀብቶች ንብረቶችን ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እንዲውሉ እንደማታደርግ ገልጻለች፡፡
ስዊዘርላንድ የሩሲያዊያንን ንብረት ለሌላ ሀገራት አሳልፋ ልትሰጥ የምትችልበት ዓለም አቀፍ አሰራር አለመኖሩንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡