ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በአሰቃቂው አደጋ “ሀቀኛ ሀገር ወዳጆችን” አጥተናል ብለዋል
በዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣናትን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ሄሊኮፕተር ተከስክሳ በጥቂቱ የ15 ሰዎች ህይወት አለፈ።
በአደጋውም በሄሊኮፕተሯ ተሳፍረው የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች እና በወደቀችበት የመኖሪያ መንደር የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ነው እየተዘገበ ያለው።
ከሟቾቹ መካከልም የዩክሬን የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ዴኒስ ሞናስትሪስኪ እና ምክትላቸው ይገኙበታል።
ሄሊኮፕተሯ በወደቀችበት የመኖሪያ መንደር ህይወታቸው ካለፉ ሰዎች መካከልም ሶስቱ ህጻናት ናቸው ተብሏል።
ፈረንሳይ ሰራሿ ሄሊኮፕተር ከኬቭ ስምንት ኪሎሜትሮች ላይ በምትገኘው ብራዞሪ ከተማ በመዋዕለ ህጻናት አቅራቢያ ነው የተከሰከሰችው።
በአደጋው ከ29 በላይ ሰዎችም መቁሰላቸውን ከከተማዋ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ማመላከታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ዘግናኝ ነው ባሉት ጥቃት “ሀቀኛ ሀገር ወዳጆችን” አጥተናል ብለዋል።
የአደጋው መንስኤ እና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተም ዝርዝር ምርምራ እንዲደረግ አዘዋል።
በዩክሬን ባለስልጣናት ይፋ የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ከ15 እስከ 22 የደረሰ ነው፤ ነገር ግን የአደጋው መንስኤን በተመለከተ አንዳቸውም ፍንጭ አልሰጡም።
የሀገሪቱ አየር ሃይል ቃል አቀባይ ዩሪይ ኢህናትም፥ የአደጋውን መንስኤ የማጣራቱ ሂደት ሳምንታትን ሊወስድ እንደሚችል ገልጸዋል።
ሩስያ ከአደጋው ጋር በተያያዘ እስካሁን ምንም አይነት መግለጫ አላወጣችም።