ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለማቅረብ በደርዘን የሚቆጠሩ የምዕራባዊያን አጋሮች ይሰበሰባሉ
አሜሪካ እና ጀርመን ለዩክሬን ታንኮችን ለማቅረብ በጋራ ሊመክሩ ነው
የአሜሪካና የጀርመን የመከላከያ አዛዦች ኪየቭ የጦርነቱን እጣ ፈንታ ሊወስን ይችላል ባለችው ከባድ ታንኮች ዙሪያ ሊነጋገሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዩክሬን ታንኮች እንዲልኩላት እየተማጸነች ነው።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስቲን ሐሙስ ዕለት የጀርመን አዲሱን የመከላከያ ሚንስትር ያገናኛሉ ተብሏል።
ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ቃል ለመግባት በደርዘን የሚቆጠሩ አጋሮች እንደሚሰበሰቡም ታውቋል።
በጀርመን በሚገኘው የአሜሪካ ራምስቴይን አየር ማረፊያ ይደረጋል የተባለው ስብሰባ ጦርነቱን በፈረንጆቹ 2023 ለማሸጋገር የሚያስችል ጦር መሳሪያ ለማቅረብ እድል ከፍቷል ተብሏል።
ዋና አጀንዳው ከባድ ታንኮችን ለኪየቭ ማቅረብ ሲሆን፤ ዩክሬን ግዛቷን ማስመለስና አዲስ የሩሲያን ጥቃት መከላከል እና መልሶ ማጥቃት እንዳለባት ተናግራለች።
የዩክሬን ፕሬዚዳንታዊ አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት አንድሪይ ኢርማክ "ጊዜ የለንም፤ ዓለም ጊዜ የላትም" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"የዩክሬን ታንኮች ጥያቄ በተቻለ ፍጥነት መዘጋት አለበት" ሲሉ አክለዋል።
"የዩክሬን ህዝብ ላለው መዘግየት ዋጋ እየከፈልን ነው። እንደዚህ መሆን የለበትም" ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ረቡዕ በዳቮስ በተካሄደው የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ለተሰበሰቡ መሪዎችን የተማጸኑ ሲሆን፤ ሩሲያ ቀጣዩን የሚሳይልና የታጠቀ የምድር ጥቃት ከማድረሷ በፊት ለሀገራቸው መሳሪያ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
የምዕራቡ ዓለም ታንኮችን ለመላክ ዋሽንግተን ከበርሊን ጋር ያላትን አለመግባባት መፍታት አለባት ተብሏል።