ለዋንጫው ቅድመ ግምት የተሰጣቸው አራት ሀገራት ጥሎ ማለፉን መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል
በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀሉ 16 ሀገራት ታውቀዋል፡፡
በውድድሩ ለዋንጫ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት እንግሊዝ ደካማ የሚባል አፈጻጸም ቢኖራትም ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏን አረጋግጣለች፡፡
በሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥታ አንድ ጨዋታ አሸንፋ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለችው እንግሊዝ በጥሎ ማለፉ በሚኖራት ጨዋታዎች ዝቅተኛ የማሸነፍ ግምት ተሰጥቷታል፡፡
ቅዳሜ በሚጀምረው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሲውዘርላንድን ከጣሊያን ሲያገናኝ አዘጋጇ ሀገር ጀርመን ከዴንማርክ ጋር የምትጫወት ይሆናል፡፡
ሶስቱን የምድብ ጨዋታዎች በማሸነፍ ዘጠኝ ነጥቦችን ሰብስባ አስደናቂ አቋም ላይ የምትገኘው ስፔን እሁድ እለት ከጆርጂያ ጋር የምትጫወት ሲሆን እንግሊዝ ደግሞ ስሎቫኪያን ትገጥማለች።
በዘንድሮ ውድድር በ7 ነጥብ በጥሩ አቋም ምድቧን በመምራት ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለችው ጀርመን ለዋንጫ ከሚቀርቡ ሁለት ቡድኖች መካከል አንዷ ልትሆን እንደምትችል ከፍተኛ ግምት አገኝታለች፡፡
ትላንት ምሽት በተደረጉ የምድብ ጨዋታ በጆርጂያ ሁለት ለዜሮ ሽንፈት ያስተናገደችው የክርስቲያኖ ሮናልዶ ሀገር ፖርቹጋል ሰኞ ከስሎቫኒያ የምትጫወት ሲሆን በተመሳሳይ ቀን ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የቤልጂየም እና ፈረንሳይ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ይደረጋል፡፡
ከየምድባቸው በሁለተኛነት ያለፉት ፈረንሳይ እና ቤልጂየም የሚያደርጉት ትንቅንቅ በጥሎ ማለፉ ተጠባቂ ጨዋታ ነው፡፡ ማክሰኞ የጥሎ ማለፉ የመጨረሻ ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን ሮማኒያ ከኔዘርላንድስ፤ ኦስትሪያ ከቱርክ ይጫወታሉ።
የዘንድሮውን ውድድር ተጠባቂ የሚያደርገው ከጥሎ ማለፉ ይልቅ በሩብ ፍጻሜ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
የእንግሊዙ ዘሰን ጋዜጣ እንዳስነበበው በውድድሩ ትልቅ ግምት የተሰጣቸው እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ስፔን ጥሎ ማለፉን የሚሻገሩ ከሆነ በሩብ ፍጻሜው የሚኖራቸው ትንቅንቅ አጓጊ ይሆናል፡፡
ለአብነትም ስፔን እና ጀርመን ወደ ጥሎ ማለፉ ከተሸጋገሩ የሚኖረውን ፍልሚያ በቀዳሚነት ጠቅሶታል፡፡
በዘንድሮው ውድድር ሶስቱን የምድብ ጨዋታዎች ያሸነፈችው ስፔን እና አዘጋጇ ሀገር ጀርመን ከሚገኙበት ጥሩ አቋም እንዲሁም አዘጋጇ ሀገር በውድድሩ ለመቆየት በምታደርገው ትግል የተነሳ የውድድሩን ምርጥ ግጥሚያ ሊያስመለክቱን ይችላሉ ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ፈረንሳይ ጥሎ ማለፉን የምትሻገር ከሆነ ከፖርቹጋል እና ከስሎቫኒያ ጨዋታ አሸናፊ ጋር የምትገናኝ ይሆናል፡፡
የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ከቅዳሜ - ማክሰኞ የሚደረጉ ሲሆን የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ደግሞ በቀጣዩ ሳምንት አርብ መከናወን ይጀምራሉ፡፡
ቅዳሜ
- ጣልያን ከ ስዊዘርላንድ
-ጀርመን ከ ዴንማርክ
እሁድ
- ስፔን ከ ጆርጅያ
- እንግሊዝ ከ ስሎቫኪያ
ሰኞ
- ፖርቹጋል ከ ስሎቬኒያ
- ፈረንሳይ ከ ቤልጅየም
ማክሰኞ
- ሮማንያ ከ ኔዘርላንድ
- ኦስትሪያ ከ ቱርክ ይጫወታሉ።