የሮናልዶዋ ፖርቹጋል ደግሞ የምባፔን ፈረንሳይ ምሽት 4 ስአት ትገጥማለች
የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ አዘጋጇ ጀርመን ከስፔን የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።
ምሽት 1 ስአት ላይ በስቱትጋርት ኤምኤችፒ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ የዘንድሮውን ሻምፒዮን የሚያመላክት ነው ተብሏል።
ጀርመን እና ስፔን በአውሮፓ ዋንጫ አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን፥ ስፔን ሁለት ጊዜ (1984 እና 2008)፤ ጀርመን ደግሞ አንድ ጊዜ (1988) አሸንፋለች።
ከ2022ቱ የኳታር የአለም ዋንጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚፋለሙት ሁለቱ ሀገራት የአውሮፓ ዋንጫን እኩል ሶስት ጊዜ አንስተዋል።
ስፔን ከጀርመን ጋር ባደረገቻቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዷ የምሽቱን ጨዋታ ተጠባቂ ያደርገዋል።
በሌላ ተጠባቂ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ፈረንሳይ ከፖርቹጋል ምሽት 4 ስአት ላይ በሀምቡርግ ቮልክስ ፓርክ ስታዲየም ይፋለማሉ።
በመኝታ ክፍሉ የሮናልዶን ምስል እያየ ያደገው ኪሊያን ምባፔ ፥ ከፖርቹጋላዊው ኮከብ ጋር ሜዳ ላይ መገናኘት “ትልቅ ክብር ነው” ብሏል።
የ25 አመቱ ወጣት በምሽቱ ጨዋታ የሚመዘገበው ውጤት ምንም ሆነ ምን ሮናልዶ የጨዋታው ኮከብ ነው ሲልም አድናቆቱን ገልጾለታል።
በግማሽ ፍጻሜው የጀርመን እና ስፔን አሸናፊ ከፈረንሳይ ወይንም ፖርቹጋል ጋር ይገናኛል።
የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ እንግሊዝ ከስዊዘርላንድ፤ ኔዘርላንድስ ከቱርክ ይጫወታሉ።