የመጀመርያው የአለም ዋንጫ በ1930 በኡራጋይ አዘጋጅነት 13 ብሔራዊ ቡድኖችን በማሳተፍ ተካሂዷል
የፊፋ አለም ዋንጫ መከናወን ከጀመረበት አመት ጀምሮ አዘጋጅ ሀገራት ለስታድየም ግንባታ ፣ ለመሰረተ ልማት ፣ . ለሆቴል እና ለሌሎችም ዝግጅት ወጪዎች በርካታ ገንዘብ መድበው ይሰራሉ፡፡
ሀገራቱ ከሚያወጡት ገንዘብ ባለፈ ውድድሩ በሚካሄድባቸው ግዚያት በተለያዩ መንገዶች ገቢ ይሰበስባሉ፡፡ በተጨማሪም አዘጋጅ ሀገራት ባህላቸውን ለአለም ለማስተዋወቅ እና ቱሪስቶችንም ለመሳብ እንደ ትልቅ አጋጣሚ ይጠቀሙበታል፡፡
የመጀመርያው የአለም ዋንጫ በኡራጋይ አዘጋጅነት በ1930 የተካሄደ ሲሆን በወቅቱ 13 ብሔራዊ ቡድኖች ተሳትፈውበታል፡፡ በአጠቃላይ 70 ግቦች በተቆጠሩበት አለም ዋንጫ አዘጋጇ ሀገር ዋንጫውን በማንሳት የመጀመርያዋ ሆናለች፡፡
በ1994 አሜሪካ ካዘጋጀችው የአለም ዋንጫ በኋላ ለውድድሩ ዝግጅት ወጪ የሚደረገው ገንዘብ ወደ ቢሊዮን ዶላሮች እየተጠጋ መጥቷል፡፡
የውድድሩ ተወዳጅነት እና ተሳታፊ ሀገራት ቁጥር እያደገ በመጣ መጠን አዘጋጅ ሀገራት ዘመናዊ ስታድየሞችን ለመገንባት እና ለአጠቃላይ ዝግጅቶች የሚመድቡት ገንዘብ እንዲጨምሩ አድርጓል፡፡
በአለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ኳታር ተወዳዳሪ የላትም፤ የ2022ቱ አለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር አዘጋጅ መሆኗ ከተረጋገጠ ጀምሮ ለ12 አመታት ባደረገችው ዝግጅት ከጥቅል ሀገራዊ ምርቷ 10 በመቶውን በየአመቱ በመመደብ ለአለም ዋንጫው ዝግጅት አድርጋለች፡፡
220 ቢሊዮን ዶላር የወጣበት የኳታር የአለም ዋንጫ በመጠኑ እስከዛሬ ለአለም ዋንጫ ከተመደቡ ገንዘቦች በ19 እጥፍ ይበልጣል፡፡