ዛሬ ምሽት 1 ስአት ፈረንሳይ ከቤልጂየም የሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ይጠበቃል
ስፔን ለ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ደረሰች።
ትናንት ምሽት 4 ስአት ላይ በተደረገ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ጆርጂያን የገጠመችው ስፔን 4 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።
ሮቢን ለ ኖርማንድ በ18ኛው ደቂቃ በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠራት ጎል ስትመራ የቆየችው ጆርጂያ፥ ሮድሪ ፋቢያን ሩይዝ፣ ኒኮ ዊሊያምስ እና ዳኒ ኦልሞ ለስፔን አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ከውድድሩ ተሰናብታለች።
የሶስት ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮኗ ጆርጂያን ማሸነፏን ተከትሎ በሩብ ፍጻሜው በአውሮፓ ዋንጫ ድል ከምትስተካከላት ጀርመን ጋር የፊታችን አርብ የምትጫወት ይሆናል።
ምሽት 1 ስአት የተደረገው ሌላኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ እንግሊዝን ለሩብ ፍጻሜ አብቅቷል።
ድራማዊ ውጤት በተመዘገበበት ጨዋታ ስሎቫኪያ ኢቫን ሽራንዝ በ25ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ስትመራ ቆይታ የጭማሪ ስአት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው(95ኛው ደቂቃ) ጁድ ቤሊንግሃም ሀገሩን ከስንብት የታደገች ወሳኝ ጎል አስቆጥሯል።
የቤሊንግሃም ጎል የጥሎ ማለፍ ግጥሚያው ወደ ጭማሪ 30 ደቂቃ እንዲያመራ ያደረገው ሲሆን፥ ሃሪ ኬን ሁለተኛዋን ግብ ከመረብ አገናኝቶ የጋሬዝ ሳውዝጌት ቡድን ሩብ ፍጻሜውን እንዲቀላቀል አድርጓል።
ውጤቱን ተከትሎም ሶስቱ አናብስት ጣሊያንን አሸንፋ ሩብ ፍጻሜውን ከተቀላቀለችው ስዊዘርላንድ ጋር ቅዳሜ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
ጀርመን እያስተናገደችው ያለው የአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ ምሽት 1 ስአት ላይ ፈረንሳይ ከቤልጂየም የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይጠበቃል።
የክርስቲያኖ ሮናልዶ ሀገር ፖርቹጋል ደግሞ ምሽት 4 ስአት ላይ ስሎቬኒያን ትገጥማለች።
የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ነገ የሚጠናቀቁ ሲሆን፥ ሮማኒያ ከኔዘርላንድስ፤ ቱርክ ከኦስትሪያ ይጫወታሉ።