በዩሮፓ ሊግ ሮማ ከሴቪያ ዛሬ ምሽት በሀንጋሪ መዲና ቡዳፔስት ይፋለማሉ
ፖርቹጋላዊው ጆሴ ሞሪንሆ ለፍጻሜ ደርሰው ተሸንፈው አለማወቃቸው ውድድሩን ተጠባቂ አድርጎታል
ሴቪላዎች በተደጋጋሚ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫ ማንሳታቸው ውድድሩን ተጠባቂ ያደረገው ሌላኛው ምክንያት ሆኗል
በዩሮፓ ሊግ ሮማ ከሴቪያ ዛሬ ምሽት በሀንጋሪ መዲና ቡዳፔስት ይፋለማሉ፡፡
በአውሮፓ ካሉ የእግር ኳስ ውድድሮች መካከል ከቻምፒዮንስ ሊግ በመቀጠል ተወዳጅ እና ፉክክክር የበዛበት ነው የዩሮፓ ሊግ ውድድር፡፡
የዚህ ውድድር የዋንጫ ጨዋታ በጣልያኑ ሮማ እና በስፔኑ ሴቪላ እግር ኳስ ክለቦች መካከል በሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስ ዛሬ ምሽት ይደረጋል፡፡
ምሽት አራት ሰዓት ላይ በሚጀመረው በዚህ ውድድር ላይ ከዚህ በፊት በተደረጉ አምስት የፍጻሜ ውድድሮች ላይ አንድም ጊዜ ያልተሸነፉት ጆሴ ሞሪንሆ ሮማን የዋንጫ አሸናፊ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ይሁንና ሴቪላዎች በዩሮፓ ሊግ በተደጋጋሚ ለፍጻሜ ደርሰው ዋንጫ ማሸነፋቸው የምሽቱ ጨዋታ ከባድ ፉክክር ሊደረግበት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ለአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ያለፉ የአውሮፓ ክለቦች እነማን ናቸው?
የሮማው አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ በፑሽካሽ አሬና ስታዲየም የሚደረገውን የፍጻሜ ጨዋታ በማሸነፍ ሮማውያንን ማስደስት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም 65 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን ከሶስት ዓመት በፊት የተካሄደውን የአውሮፓ ሱፐር ካፕ የፍጻሜ ውድድርን አስተናግዷል፡፡
ሴቪላ እግር ኳስ ክለብ ስድስት ጊዜ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን የበላ ሲሆን ሮማ ደግሞ ባሳለፍነው ዓመት የዩሮፓ ሱፐር ካፕ ውድድርን ዋንጫ አሸንፏል፡፡
የዛሬ ምሽት የፍጻሜ ውድድሩን እንግሊዛዊው ዳኛ አንቶኒ ቴይለር በመሀል ዳኝነት እንደሚመሩት ተገልጿል፡፡
የዩሮፓ ሊግ የቀጣይ አመት የፍጻሜ ውድድር በአየርላንድ ደብሊን እንደሚካሄድ ሲገለጽ የ2025 ዓመት የዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ ውድድር ደግሞ በስፔን ቢልባኤ ሳን ማሜስ ይካሄዳል ተብሏል፡፡