ተወዳጁ የአውሮፓ ሀገራት እግር ኳስ ውድድሮች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል
የጣልያኑ ናፖሊ ከ30 ዓመት በኋላ ወደ ዋንጫ ሲመለስ በሌሎቹ ሀገራት ግን የተለመዱ ቡድኖቸ ዋንጫ አንስተዋል
የጀርመኑ ቦሪሺያ ዶርትሙንድ በመጨረሻ ዋንጫውን በሙኒክ ተነጥቆ ዓመቱን በሀዘን አጠናቋል
ተወዳጁ የአውሮፓ ሀገራት የውስጥ ሊግ ውድድሮቻቸውን አብዛኞቹ ትናንት አጠናቀዋል፡፡
በዚህ የመዝጊያ ውድድሮች ላይ አይረሴ ትንቅንቆች የተደረጉ ሲሆን በአንግሊዝ ወደ ታችኛው ሊግ ላለመውረድ፣ በጀርመን የውድድር ዓመቱን ዋንጫ ለማሸነፍ በጣልያን ደግሞ ለአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት ከባድ ፉክክር ተደርገዋል፡፡
እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ አሸናፊው ባልተለየበት የጀርመን ቡደንሊግ ውድድር ላይ ቦሪሺያ ዶርትሙንድ እጁ ላይ ያለውን እድል አሳልፎ ለተቀናቃኙ ባየርን ሙኒክ ሰጥቷል፡፡
ዶርትሙንድ ዋንጫውን ለመብላት ማሸነፍ ብቻ በቂው የነበረ ቢሆንም በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ የነበረው ባየርን ሙኒክ ማሸነፉን ተከትሎ በአንድ ነጥብ በመብለጥ የዘንድሮውን ዋንጫ አሸንፏል፡፡
እንግሊዛውዊ ቤሊንግሀም የዘንድሮው ውድድር ኮኮብ ተጫዋች በመባል ሲመረጥ የአርቢ ላይፕዚሹ ክርስቶፈር ንኩንኩ በ16 ጎል ኮኮብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል፡
አር ቢ ላይፕዚሽ እና ዩኒየን በርሊን ሶስተኛ እና አራተኛ ሆነው በማጠናቀቅ በቀጣይ ዓመት በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ናፖሊ ከ30 ዓመት በኋላ የዘንድሮውን የጣልያን ሴሪ ኤ ውድድርን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ላዚዮ፣ ኢንተር ሚላን እና ኤሲ ሚላን ደግሞ ለቻምፒዮንስ ሊግ ያለፉ ክለቦች መሆን ችለዋል፡፡
የናፖሊው አጥቂ ናይጀሪያዊው ቪክተር ኦስሜን 25 ጎሎችን በማስቆጠር የዘንድሮው የጣልያን ሴሪኤ ኮኮብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል፡፡
አርሰናል ለረጅም ወራት ሊጉን ሲመራ ቆይቶ ሸንፈቶችን ማስተናገዱን ተከትሎ በመጨረሻም ዋንጫውን ለማንችስተር ሲቲ መስጠቱ የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዋነኛ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ለአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ያለፉ ክለቦች ሲሆኑ ሊድስ ዩናይትድ እና ሌይሰተር ክለቦች ሳውዛምፕተንን ተከትለው ወደ ሁለተኛ ሊግ ውድድር የወረዱ ክለቦች ሆነዋል፡፡
የማንችስተር ሲቲው አጥቂ አርሊንግ ሆላንድ በ36 ጎሎች የዘንድሮውን ውድድር የሊጉ ኮኮብ ግብ አግቢ፣ ኮኮብ ተጫዋች እና ምርጥ ወጣት ተጫዋች ሽልማቶችን ጠራርጎ ማሸነፉ ተገልጿል፡፡
በስፔን ደግሞ ባርሴሎና ከነበረበት ምስቅልቅሎሽ በመውጣት የዘንድሮውን የላሊጋ ዋንጫ ሲያነሳ ሪያል ማድሪድ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ሶሴዳድ ወደ አውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ ችለዋል፡፡
ሮበርት ሌዋንዶውስኪ በ23 ጎሎች የስፔን ላሊጋን በኮኮብ ግብ አግቢነት ሲያጠናቅቅ ካሪም ቤንዜማ በ18 ጎሎች ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
ብዙ ፉክክሮች የሉበትም በሚባለው የፈረንሳይ ሊግ አንድ ውድድር እንደተለመደው ፒኤስጂ ዋንጫውን ሲወስድ ሌንስ፣ ማርሴይ እና ሊል ደግሞ ለአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ያለፉ ክለቦች ሆነዋል፡፡
ክሊያን ምባፔ የሊግ አንድ ኮኮብ ተጫዋች ሲባል በ28 ጎሎች ኮኮብ ግብ አግቢነትንም አሸንፏል፡፡