በአውሮፓ አስከ ቀጣዩ የካቲት ድረስ 500 ሺህ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሊሞቱ ይችላሉ ተባለ
በአውሮፓ 47 በመቶዎቹ ብቻ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ወስደዋል
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአውሮፓ ከሁሉም አህጉራት ከፍተኛው ነው
በአውሮፓ አስከ ቀጣዩ የካቲት ድረስ 500 ሺህ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሊሞቱ ይችላሉ ተባለ።
በዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ቢሮ ባወጣው መግለጫ በአውሮፓ እስከ ቀጣዩ የካቲት ድረስ ግማሽ ሚሊየን ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ ብሏል።
በድርጅቱ የአውሮፓ ቢሮ ዳይሬክተር ሀንስ ክሉግ እንዳሉት በአውሮፓ አሁን ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አደገኛ መሆኑን ገልጸው የቫይረሱ ጥቃት በዚሁ ከቀጠለ ከአራት ወራት በኋላ 500 ሺህ ዜጎች ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል ብለዋል።
ቫይረሱ በአውሮፓ አህጉር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ 78 ሚሊዮን ዜጎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን እንግሊዝ፣ሩሲያ፣ቱርክ እና ፈረንሳይ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቁ አገራት ናቸው።
በነዚህ አገራት በቫይረሱ የተጠቁ ዜጎች ቁጥር በአፍሪካ፣በደቡብ ምስራቅ እስያ፣ በደቡብ ፓስፊክ እና በምስራቅ ሜዲትራኒያን አካባቢዎች ባሉ ሀገራት ካሉት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች እንደሚበልጥም ተገልጿል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በተያዘው ሳምንት በቫይረሱ ተይዘው ወደ ሆስፒታል የገቡ ዜጎች ቁጥር ባሳለፍነው ሳምንት ካለው ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ ሲጨምር፤ የሟቾች ቁጥር ደግሞ በ12 በመቶ ጨምሯል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ባሳለፍነው ሳምንት 12 ሺህ የነበረ ሲሆን፤ እስከ ትናንት ድረስ ግን ወደ 24 ሺህ ከፍ ማለቱ እንዳሳሰባቸው ዳይሬክተሩ አክለዋል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን መውሰድ ዋነኛው ቢሆንም በአውሮፓ ክትባቱን የወሰዱ ዜጎች ግን 47 በመቶ ብቻ ናቸው።
ዘጠኝ ሀገራት ግን 70 በመቶ ዜጎቻቸውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሲሰጡ በዩክሬን፣ በኪርጊስታን እና በአርመኒያ ደግሞ ክትባቱን የወሰዱ ዜጎቻቸው ቁጥር ከ20 በመቶ በታች ናቸው።
የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን በሁሉም አህጉራት የተከሰተ ቢሆንም ከአውሮፓ ውጪ ባሉ አህጉራት የቫይረሱ ስርጭት መጠነኛ መቀነስ ማሳየቱን የዓለም ጤና ድርጅት በሳምንታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል።
በአውሮፓ ከ100 ሺህ ህዝብ መካከል 192 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ እንደሚያዙ ጥናችም ያመላክታሉ።