በኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ተባለ
በዚሁ ሳምንት በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ውስጥ 737 ያህሉ ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል መግባታቸው ተገልጿል
በአንድ ሳምንት ውስጥም 158 ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል ተብሏል
በኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን አስታውቋል።
- በኢትዮጵያ ሦስተኛ ዙር የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስለ መከሰቱ ማሳያዎች ተገኝተዋል ተባለ
- በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር ከ111 ቀናት በኋላ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል
ባሳለፍነው ሳምንት ዴልታ የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በኢትዮጵያ መኖሩ መረጋገጡ ይታወሳል።
ይህ የቫይረስ ዝርያ በስርጭት ፍጥነት ቀደም ብሎ ከነበሩት አልፋ እና ቤታ ዝርያዎች በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ መረጃዎች ያሣያሉ፡፡
የዴልታ ቫይረስ ዝርያ በአለም ላይ ከተከሰተ ጀምሮ በበሽታው የሚያዙ፣ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡና ህይዎታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ አሁናዊ የስርጭት ሁኔታ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 9 ሺህ 164 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
እነዚህ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ከመያዛቸውም በላይ በሳምንቱ ቀናት በአማካይ 737 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል ገብተው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ ብሏል ኢንስቲትዩቱ።
እንዲዲሁም 158 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በተጠቀሰው ሳምንት በአማካይ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ 17 ነጥብ 7 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህም ከላፈው ሳምንት ሲነጻጸር መጨመሩን ያሳያል ተብሏል።
በሌላ በኩል በአማካይ የሞት ምጣኔ 1 ነጥብ 6 በመቶ የደረሰ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ማለትም መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ/ም 38 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ከ147 ቀናት በኋላ የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ወደ ጽኑ ሕሙማን ገብተው ክትትል የሚደረግላቸው ሰዎች ደግሞ 751 ደርሰዋል፡፡ይህም ከ134 ቀናት በኋላ የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል፡፡
በመሆኑም ቫይረሱ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመከላከል የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ማድረግ እና የኮቪድ-19 ክትባት መውሰድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ሲል ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
በተለይም የተቀመጡ መመሪያዎችን ያላገናዘቡ ስብሰባዎች፣ ስልጠናዎች፣ በተጨናነቀ መልኩ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚሳተፍባቸው ሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ የአደባባይ በዓላት ላይ ርቀትን የመጠበቅ፣ማስክ የማድረግ እና የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር ወይም በሳሙናና ውሃ የእጅን ንጽህና መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ግዴታም ጭምር መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ አስካሁን ለ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንደተሰጣቸው ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የመንግስት ጤና ተቋማት ክትባቱ በነፃ ስለሚሰጥ ከ18 ዓመት በላይ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል አቅራቢያቸው በሚገኝ የመንግስት ጤና ተቋማት በመሄድ መከተብ እንደሚገባቸው ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።