“አውሮፓ ከአራት ዓመታት በኋላ በኋይት ሀውስ ወዳጅ አገኘች” የአውሮፓ ሕብረት
የዓለም ሀገራት መሪዎች በአዲሱ የአሜሪካ አስተደዳር ደስተኞች መሆናቸውን እየገለጹ ነው
“ትራምፕ የዓለምን ጠንካራ ዴሞክራሲ ሲያበላሹት መቆየታቸውን ተገንዝበናል” የስፔን ጠ/ሚ ፔድሮ ሳንቼዝ
የዓለም ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች ለ46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የደስታ መግለጫ መላካቸውን ቀጥለዋ፡፡ አንዳንዶቹ የዶናልድ ትራም አስተዳደር “እጅግ አስከፊ ነበር” ያሉ ሲሆን ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ፣ የባይደን ወደ ኃላፊነት መምጣት “ዴሞክራሲ ጽንፈኝነትን ማሸነፉን” እንደሚያመለክት ገልጸዋል፡፡ ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ ፣ “ትራምፐ ከአምስት ዓመታት በፊት እየቀለዱ እንደነበር ብናስብም፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ የዓለምን ጠንካራ ዴሞክራሲ ሲያበላሹት መቆየታቸውን ተገንዝበናል” ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ለይን “ከአራት ዓመት በኋላ አውሮፓ በኋይት ሀውስ ወዳጇን አገኘች“ ሲሉ የትራምፕ አስተዳደር በሕብረቱ እና በአሜሪካ መካከል ልዩነትን መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ በካፒቶል ሂል የተካሄደው “የባይደን በዓለ ሲመት የአሜሪካ ዴሞክራሲ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ አመላካች ነው” ሲሉም ሊቀመንበሯ ገልጸዋል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው “አውሮፓ በአሜሪካ ላይ አላግባብ መጠቀም ይፈልጋል፤ ይህንን መፍቀድ የለብንም“ የሚል ንግግር አሰምተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ “የብራሰልስ ወዳጆቻችን እኛን በሚገባ እያስተናገዱን አይደለም“ በሚል ቅርታ አሰምተውም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የብራሰልስና የዋሺንግተን ግንኙነት መሻከሩ ይታወሳል፡፡
የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴይንሜየር “የዓለም ትልቁ ዴሞክራሲ በሕዝበኝነት ሴራ ስር እንደነበረ አይተናል“ ብለዋል፡፡ በዓለም ላይ ያለውን ጽንፈኝነት “መቃወም አለብን“ ያሉት የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፣ የትራምፕን አስተዳደር “ጽንፈኝነትን ያበረታታና ወዳጅነትን ያላስቀደመ ነበር“ ብለዋል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ፣ የባይደን ወደ ኃላፊነት መምጣት ለትራንስ አትላንቲክ ሕብረት አዲስ ምዕራፍ ነው ሲሉ የአሜሪካን አዲስ አስተዳደር አድንቀዋል፡፡ ኔቶ ከባይደን አስተዳደር ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡
የዓለም ሀገራት መሪዎች በአዲሱ የአሜሪካ አስተደዳር ደስተኞች መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡ በተቃራኒው አሜሪካን ለአራት ዓመታትን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ትራምፕ በብዙዎች ሲወገዙ እየተሰማ ነው፡፡