ቭላድሚር ፑቲን ለጆ ባይደን ‘የእንኳን ደስ አለዎት’ መልዕክት አስተላለፉ
ሩሲያ የደስታ መልዕክት ለማስተላለፍ የጆ ባይደን አሸናፊነት በይፋ እስኪረጋገጥ ስትጠብቅ ነበር
አሜሪካና ሩሲያ በዓለም ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የተለየ ኃላፊነት አንዳለናቸው ፑቲን ገልጸዋል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸው ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የደስታ መግለጫ ሳይልኩ የቆዩት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ የደስታ መግለጫ ልከዋል፡፡
ምንም እንኳን የዓለም መሪዎች ለባይደን ‘የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት’ ወዲያው በትኩሱ ቢያስተላልፉም ፣ አሸናፊነታቸው በይፋ እስኪገለጽና የአሜሪካ ውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻ እስከሚጠናቀቅ መታቀብን በመምረጥ ነበር ሩሲያ በዝምታ የቆየችው፡፡
በትናንትናው ዕለት በ‘ኤሌክቶራል ቮት’ ምርጫ ጆ ባይደን ፕሬዝዳንትነታቸው መረጋገጡን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ፑቲን ከሞስኮ የደስታ መግለጫ የላኩላቸው ሲሆን ፣ ዋሺንግተንና ሞስኮ ያለባቸውን ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮ በጋራ እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡
ፑቲን ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው በዓለም ላይ አሁን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ከተመራጩ ፕሬዚዳንት ጋር በጋራ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው “ዋሺንግተንና ሞስኮ ለዓለም ሰላምና መረጋጋት የተለየ ኃላፊነት አለባቸው” ያሉት ፑቲን ዓለማችን የተደቀኑባትን ችግሮች ከተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጋር ሆነው እንደሚፈቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከተካሔደ በኋላ በየግዛቱ በጥቂት ተወካዮች በሚካሔደው የውክልና ድምጽ ምርጫ ከ538 የውክልና ድምጾች 306 ድምጽ በማግኘት ጆ ባይደን ትናንት ምሽት በይፋ የአሜሪካ 46ኛ ፕሬዝዳንትነታቸው ተረጋግጧል፡፡ ‘ኤሌክቶራል ኮሌጁ’ ማሸነፋቸውን ካረጋገጠላቸው በኋላ ጆ ባይደን ባደረጉት ንግግር “የሕግ የበላይነት ፣ ህገ-መንግስታችን እና የህዝብ ፍላጎት አሸንፈዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‘ኤሌክቶራል ኮሌጅ’ የሚል ስያሜን በያዙት በእነዚህ የውክልና መራጮች ከሚሰጠው ድምጽ ውስጥ 270 እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን ማግኘት ለአሸናፊነት የሚያበቃ ሲሆን ባይደን በዋናው ምርጫ ያገኙትን ያክል 306 ድምጽ አግኝተዋል፡፡