አውሮፓን እያነደደ ያለው ሰደድ እሳትና ሙቀት በፍጥነት አተስፋፋ መሆኑ ተገለጸ
በፈረንሳይ ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ የወይን ማሳዎች በእሳቱ ወድመዋል
ስፔን፣ፖርቹጋል ፣ጣልያን ግሪክና እንግሊዝ የሰደድ እሳቱ የተከሰተባቸው ሀገራት ናቸው
አውሮፓን እያነደደ ያለው ሰደድ እሳትና ሙቀት በፍጥነት አተስፋፋ በስፔን በኩል አድርጎ ወደ አፍሪካ በመግባት ላይ ይገኛል።
በደቡብ አውሮፓ ሀገራት በተነሳው ሰደድ እሳት እና አደጋውን ተከትሎ በሚፈጠረው ሙቀት የሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል።
የደቡባዊ አውሮፓ ሀገራት የሖኑት ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ግሪክ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣልያን እየተስፋፋ ባለው ሰደድ እሳት ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
ሰደድ እሳቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በፖርቹጋል ሲሆን፤ አሁን ላይ ወደ ጎረቤት ሀገራት በመስፋፋት እና ለበርካታ ዜጎች ስጋት መሆን መቻሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
በፖርቹጋል እስካሁን በእሳቱ እና በተፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት 238 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ደን በእሳቱ መውደሙ ተገልጿል።
70 የሚሆኑ የፖርቹጋል ከተሞች በዚሁ ሰደድ እሳት እና ሙቀት የተጎዱ ሲሆን እስካሁን በአምስት ቦታዎች ሰደድ እሳቱ ተከስቶ መንግሥት እና ህዝቡ እሳቱን ለማጥፋት በመረባረብ ላይ ይገኛል።
ከአንድ ሺህ በላይ የድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች እየጣሩ ባለበት በሰሜናዊ ፖርቹጋል ውሀ እና ኬሚካል ይረጭ የነበረ አንድ አውሮፕላን ሲከሰከስ አብራሪው ህይወቱ አልፏል ተብሏል።
በፈረንሳይ ደግሞ ከ34 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲገቡ ተደርጓል።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጌራልድ ዳርማኒን 19 ሺህ ሄክታር የወይን ማሳዎች በእሳት መውደሙን ተናግረው በደቡባዊ ፈረንሳይ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ወደ ተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ሁሉም የደቡብ አውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ ሙቀትን እያስተናገዱ ሲሆን ሙቀቱ በፖርቹጋል 47 ድግሪ ሴንትግሬድ፣ በስፔን፣ እንግሊዝ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ከ40 ድግሪ ሴንትግሬድ በላይ ሙቀት በመመዝገብ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
እሳቱ ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን እንዳቃጠለ የተናገሩት የፖርቹጋል ባለስልጣናት ሙቀቱን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን በማጣት ላይ እንደሆኑ ተጠቅሷል።
የፖርቹጋል አዋሳኝ የሆኑ የስፔን ቦታዎች በዚሁ እሳት ጉዳቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆኑ መኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በመውደም ላይ ናቸው ተብሏል።
በስፔን ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ ደን ሲቃጠል ከ50 በላይ ከተሞች በዚሁ እሳት ተጎድተዋል ተብሏል።
የእሳት አደጋው በስፔን እየሰፋ መምጣቱ በሞሮኮ በኩል አድርጎ ወደ አፍሪካ መግባቱ የታወቀ ሲሆን ሞሮኮ ለስፔን በቀረቡ ቦታዎች ነዋሪዎቿን ማውጣት መጀመሯን አስታውቃለች።