በደቡብ አውሮፓ ሀገራት በተነሳው ሰደድ እሳት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 238 ደረሰ
ስፔን፣ፖርቹጋል ፣ጣልያን ግሪክ፣ እና ፈረንሳይ የሰደድ እሳቱ የተከሰተባቸው ሀገራት ናቸው
ሰደድ እሳቱ በስፔን በኩል አድርጎ ወደ አፍሪካ ሊገባ እንደሚችል ተሰግቷል
በደቡብ አውሮፓ ሀገራት በተነሳው ሰደድ እሳት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 238 ደረሰ፡፡
የደቡባዊ አውሮፓ ሀገራት የሖኑት ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ግሪክ፣ ፈረንሳይ እና ጣልያን እየተስፋፋ ባለው ሰደድ እሳት ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሰደድ እሳቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠከሰተው በፖርቹጋል ሲሆን አሁን ላይ ወደ ጎረቤት ሀገራት በመስፋፋት እና ለበርካታ ዜጎች ስጋት መሆን መቻሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በፖርቹጋል እስካሁን በእሳቱ እና በተፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያ 238 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ደን በእሳቱ መውደሙ ተገልጿል፡፡
በሰሜናዊ ፖርቹጋል የተከሰተውን እሳት ለመቆጣጠር ውሀ እና ኬሚካል ይረጭ የነበረ አንድ አውሮፕላን ሲከሰከስ አብራሪው ህይወቱ አልፏል ተብሏል፡፡
እሳቱ በደቡባዊ ፈረንሳይ የተከሰተ ሲሆን ሀገሪቱ እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ ዜጎቿን ከአካባቢው በማውጣት ከአደጋው እንዲተርፉ ማድረጓ ተጠቅሷል፡፡
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጌራልድ ዳርማኒን 10 ሺህ ሄክታር መሬት በእሳት መውደሙን ተናግረው በደቡባዊ ፈረንሳይ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ወደ ተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ሁሉም የደቡብ አውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ ሙቀትን እያስተናገዱ ሲሆን ሙቀቱ በፖርቹጋል 47 ድግሪ ሴንትግሬድ፣ በስፔን ከ40 ድግሪ ሴንትግሬድ በግሪክ እና በጣልያንም ከፍተኛ ሙቀት በመመዝገብ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እሳቱ ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን እንዳቃጠለ የተናገሩት የፖርቹጋል ባለስልጣናት ሙቀቱን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን በማጣት ላይ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የፖርቹጋል አዋሳኝ የሆኑ የስፔን ቦታዎች በዚሁ እሳት ጉዳቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆኑ መኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በመውደም ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
አደጋውን ለመቆጣጠርም በርካታ ጥረቶች በመካሄድ ላይ ቢሆኑም ሰደድ እሳቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡
የእሳት አደጋው በስፔን እየሰፋ መምጣቱ በሞሮኮ በኩል አድርጎ ወደ አፍሪካ እንዳይገባ ስጋት ያለ ሲሆን ሞሮኮ ለስፔን በቀረቡ ቦታዎች ነዋሪዎቿን ማውጣት መጀመሯን አስታውቃለች፡፡