የአውሮፓ ትልቁ የሮተርዳም ወደብ “በኮኬይን ተጥለቅልቋል” ተባለ
የወደብ ባለስልጣናት ከላቲን አሜሪካ የሚመጡትን ኮንቴይነሮች ላይ የተሟላ ቅኝት እንዲያካሂዱ ተጠይቀዋል
እጽ አዘዋዋሪዎች ኮኬይን በሮተርዳም በኩል ለመላክ ውስብስብ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ይገለጻል
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኮንቴይነሮች የሚያስተናግደውና የአውሮፓ መግቢያ በር ተደርጎ የሚቆጠረው ትልቁ የሮተርዳም ወደብ ዋና የኮኬይን ማስተላለፊያ ድልድይ እየሆነ መምጣቱ እየተነገረ ነው፡፡
ኮኬይኖቹ ብዙውን ጊዜ በኮንተይነሮች ውስጥ በመደበቅ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ከውኃው መስመር በታች ባሉት ክፍት ቦታዎች ውስጥ በመርከቦች ስር በማስቀመጥ ወደ አውሮፓ ምድር እንዲዘልቁ እደደሚደረጉም ይገለጻል፡፡
ይህም በአውሮፓ ምድር ከፍተኛ የኮኬይን እጽ ስርጭት መኖሩ የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
ኔዘርላንድ በአውሮፓ ትልቁ በሆነው ወደብ ከፍተኛ ጭነት ያለባቸው ክሬኖች ከሚያስተናግዱ ሀገራት አንዷ ናት፡፡
በወደቡ የጉምሩክ ኦፊሰሮች ቡድን የሚመሩት ጌር ሼሪንጋ እንደሚሉት ከሆነ እንደፈረንጆቹ በ2021 ብቻ ወደ 70 ቶን የሚጠጋ ኮኬይን ተይዟል ይህም በ2020 ከነበረው በ74 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡
በአጎራባቿ ቤልጂየምም ቢሆን ከፍተኛ የሆነ የኮኬይን መጠን በቁጥጥር ስር እንደሚውል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በአውሮፓ የሚስተዋለው የኮኬይን መጥለቅለቅ “አሳሳቢ ጉዳይ ነው” የሚሉት ጌር ሼሪንጋ፤ በአውሮፓ ውስጥ "ብዙ ገዢዎች ያሉ ይመስላል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"ፍላጎት ካለ አቅርቦት አለ " እንደማለት ነውም ብለዋል፡፡
ሮተርዳም በተለይ የጉምሩክ ፍተሻዎችን በማሳደግ ወደ አውሮፓ የሚያደርገውን ነጭ ዱቄት ለማስቆም ዋና ዋና እርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል ጌር ሼሪንጋ።
ነገር ግን ሰዎች ኮኬይን መጠቀማቸውን እስከቀጠሉ ድረስ ችግሩ በ2022 መፍትሄ ያገኛል ብለው እንዳማያስቡ አምነዋል።
ጌር ሼሪንጋ ይህን ይበሉ እንጅ የሮተርዳም ከንቲባ የእሳቸውን ኃሳብ የሚቃወም አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
የሮተርዳም ከንቲባ አህመድ ኦታሌብ የወደብ ከተማዋ "በኮኬይን ተጥለቅልቃለች" የሚለውን እውነታ ተቃውመዋል፡፡
ይሁን እንጅ የወደብ ባለስልጣናት ከላቲን አሜሪካ የሚመጡትን ኮንቴይነሮች ላይ የተሟላ ቅኝት እንዲያካሂዱ ጠይቀዋል ከንቲባው፡፡
የወደብ ፖሊስ የአደንዛዥ እጽ ስፔሻሊስት የሆነችው ሮሚልዳ ሻፍ እንዳለችው፤ እጽ አዘዋዋሪዎች ኮኬይን በሮተርዳም በኩል ለመላክ እና በኋላም መልሶ ለማግኘት ውስብስብ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።
በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ኮንቴይነሮች ውስጥ የኮንትሮባንድ እጾች ማግኘት "በእርግጥ በሳር ውስጥ መርፌ የማግኘት ያክል ነው" ስትልም ነው ሮሚልዳ ሻፍ ለኤኤፍፒ የተናገረችው።