ፕሬዝዳንት ዢ የዩክሬንን ችግር በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት ለሀገራት የጋራ ጥቅም ነው ብለዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ እና የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ሚሼል በዩክሬን መረጋጋት እንዲፈጠር ጥሪ አቀረቡ
የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት ለማስቆም ተጽዕኖ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሐሙስ እለት በቤጂንግ የተካሄደው የሁለቱ መሪዎች ውይይት ከሶስት ሰአት በላይ የፈጀ ሲሆን በሰብአዊ መብቶች፣ በታይዋን ጉዳይ፣ በንግድ ግንኙነቶች እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
ቻርለስ ሚሼል በጋዜጣዊ መግለጫቸው " ፕሬዝዳንት ዢን በሩስያ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ተጠቅመው ሞስኮ የመንግስታቱን ድርጅት ቻርተር እንድታከብር አሳስቤአለሁ" ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ቃል አቀባይ እንደተናገሩት "ሁለቱም መሪዎች የኒውክሌር ስጋቶች ኃላፊነት የጎደላቸው እና በጣም አደገኛ ናቸው" ብለዋል።
ሲሲቲቪ ፕሬዝዳንት ዢ “የዩክሬንን ችግር በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት ለአውሮፓ ህብረት እና ለአውሮፓ-እስያ ሀገራት የጋራ ጥቅም የሚጠቅም ነው” ማለታቸውን ዘግቧል።
“አሁን ባለው ሁኔታ ቀውሱን መባባስና መስፋፋትን አስወግደን ለሰላም መስራት አለብን” ብለዋል ዢ።
ሚሼል በቻይና አንድ ቀን ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬፒያንግ እና ከብሔራዊ ህዝባዊ ኮንግረስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሊ ዣንሹ ጋር ተገናኝተዋል።
የዢና የሚሼል ንግግር 27ቱ የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በቻይና ላይ የሶስት ሰአታት የፈጀ ስልታዊ ውይይት ካደረጉ ከስድስት ሳምንታት በኋላ መሆኑን ዩሮኒውስ ዘግቧል።
ቻይና፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት ላለማውገዝ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ለውይይቱ መነሻ መሆኑ ተነግሯል።