የኑሮ ውድነቱ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተከሰተ ነው ተብሏል
የኑሮ ውድነት ያማረራቸው አውሮፓውያን የስራ ማቆም አድማቸውን ቀጥለዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት ማቅናታቸውን ተከትሎ የዓለም ነዳጅና ምግብ ዋጋ እያሻቀበ ሲሆን፤ ጦርነቱ የዓለምን የምርት አቅርቦት እና የዋጋ መዛነፍን አስከትሏል።
ሩሲያ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ ፍላጎት የምትሸፍን ቢሆንም፤ ምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን በመጣል መሆናቸውን ተከትሎ በአውሮፓ በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የምርቶች ዋጋ ጨምረዋል።
በዚህና ሌሎች ምክንያቶች በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ እና አቅርቦት በመጨመሩ ዜጎች መንግስቶቻቸው የተለያዩ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ እርምጃዎች እንዲወስዱላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
ይሄንን ተከትሎም በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ ያሻቀበ ሲሆን ሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያዎች እንዲደረግላቸው በተለያዩ መንገዶች በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
የሆላንድ የባቡር ትራንስፖርት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
ከ115 ሺህ በላይ የብሪታንያ ፖስታ ቤት ሰራተኞችም ደመወዝ እንዲጨመርላቸው የስራ ማቆም አድማ መምታታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የፖስታ ቤት ሰራተኞቹ ለቀጣዮቹ አራት ቀናት የስራ ማቆም አድማ እንደሚመቱ አስቀድመው ያስጠነቀቁ ሲሆን በዛሬው ዕለት የመጀመሪያውን ስራ ማቆም አድማ አድርገዋል።
ባለፈው ሳምንት የብሪታንያው ፌሊክስቶው ወደብ አገልግሎት ሰራተኞች ደመወዝ እንዲጨመርላቸው የስምንት ቀናት አድማ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በብሪታንያ ካሉ የወደብ አገልግሎት ከሚሰጡ መሰል ተቋማት መካከል ትልቁ የሆነው የዚህ ተቋም ማሽን ኦፕሬተሮች፣ የክሬን አሽከርካሪዎች እና ሌሎች ሰራተኞች ስራ አቁመዋል ተብሏል።
በብሪታንያ ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው በአድማ ሲጠየቅ የአሁኑ የመጀመሪያው ያልሆነ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት የባቡር ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ከአንድ ወር በፊት ተመሳሳይ ነገር አድርገው ነበር።
በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች ወጪያቸውን ለመቀነስ በሚል የትምህርት ቀናትን አሁን ካለበት ወደ ሶስት ቀናት ዝቅ ለማድረግ ምክክር መጀመራቸው ባሳለፍነው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።
የጀርመኑ ግዙፍ የአቪየሽን ኩባንያ ሉፍታንዛ ሰራተኞችም ደመወዝ እንዲጨመርላቸው በጠሩት የስራ ማቆም አድማ ከአንድ ሺህ በላይ በረራዎቹን መሰረዙ አይዘነጋም።