ሶስት ሀገራት ከአፍሪካ ወደ አውሮፖ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ተስማሙ
ናይጀሪያ፣ ኒጀርና አልጀሪያ ነዳጅ ወደ አውሮፓ ለማስተላለፍ ተስማምተዋል
የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ አውሮፓ ከሩሲያ ጥገኝነት የማላቀቁ አንድ አካል ነው ተብሏል
ሶስት ሀገራት ከአፍሪካ ወደ አውሮፖ የነዳጅ መስመር ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ተስማሙ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ በሩሲያ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የነበሩ የአውሮፓ ሀገራትን ጎድቷል።
የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም በሚል ማዕቀብ ቢጥሉም የነዳጅ እጥረቱ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸው ይገኛል።
በዚህም መሠረት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የነዳጅ ሀብት ያላቸው የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ሀገራትን እንደ አማራጭ በማማተር ላይ ናቸው።
የዚህ አንድ አካል የሆነው እቅድ ከምዕራብ አፍሪካ ተነስቶ ወደ ሰሜን አፍሪካ የሚያቀና ከዚያም ወደ አውሮፓ ነዳጅን ማስተላለፍ የሚያስችል መስመር ለመገንባት ስምምነት ተፈጽሟል።
ስምምነቱ በናይጀሪያ፣ ኒጀር እና አልጀሪያ ሀገራት መካከል መፈጸሙን ቢቢሲ ዘግቧል።
በዚህ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር አማካኝነት በዓመት 30 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነዳጅ በዓመት ወደ አውሮፓ ለማጓጓዝ መታቀዱም ተገልጿል።
4 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚኖረው የተገለጸው ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር 13 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ተብሏል።
ይሁንና ይህን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመርን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ወጪ ማን እንደሚሸፍን፣ ግንባታው መቼ እንደሚጀመር እና መቼ እንደሚጠናቀቅ ይፋ አልተደረገም።