ጦርነቱን ተከትሎ በመደፈሯ ልትመሰርት የነበረው ትዳር የቀረባት ወጣት አሳዛኝ ታሪክ
የቻለ የአቅሙን እንዲደግፋትም ጠይቃለች
በደረሰባት አስከፊ ጥቃት ልቧ የተሰበረው ሉባባ ወደ ትውልድ ቀዬዋ ለመመለስ ሳትችል ቀርታለች
ወጣት ሉባባ የ21 ዓመት ወጣት ነች፡፡ በደረጃ አራትም ከቴክኒክና ሙያ ብትመረቅም ስራ በማጣቷ ወላጆቿን አስቸግራ በምርሳ ከተማ የጉሊት ንግድ ስራ ከጀመረች ሁለት ዓመት አልፏታል፡፡
ስራዋም እየታወቀ ደንበኞቿም እየተበራከቱ ሲመጡ ንግዷን የማሻሻል እንዲሁም በእስልምና ሀይማኖት ስርዓት መሰረት ከፍቅር ጓደኛዋ ጋር በኒካህ ትዳር የመመስረት እቅድም ነበራት፡፡
ወቅቱ ክረምቱ አልፎ አዲሱ የ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመት የገባ ቢሆንም የበዓል ድባብ በአካባቢው ከራቀ ሰንብቷል፡፡ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የትግራይ ክልል መዲና መቀሌን መልቀቁን ተከትሎ በአማራ ክልል አዋሳኝ ዞኖች የጦርነት ድባብ፣ የከባድ መሳሪያ ተኩስ እና ሌሎችም ረፍት የሚነሱ ወሬዎች ከዚያም ከዚህም መሰማት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡
የሕወሓት ታጣቂዎችም የጀመሩትን ዉጊያ አጠናክረው ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመዝለቅ የሰሜን ወሎ ከተሞችን እና ወረዳዎችን መቆጣጠር ጀምረዋል፡፡ እያየለ በመጣው የታጣቂዎቹ ጥቃት ሰለባ ከሆኑና ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ከደረሰባቸው የአካባቢው ከተሞች መካከልም አንዷ መርሳ ነበረች፡፡
በአነስተኛ የጉሊት ንግድ ስራ ትተዳደር የነበረችው የ21 ዓመቷ ሉባባ ኢብራሂም (ለደህንነቷ ሲባል ስሟ የተቀየረ)ም የጦርነቱ ሰለባ በሆነችው በዚህች ከተማ በመርሳ ትኖር ነበረ፡፡
የሕወሓት ታጣቂዎች መርሳ ከተማን ይቆጣጠራሉ ብላ ባልጠበቀችው መንገድ እና ፍጥነት ከተማዋን መስከረም ወር 2014 ዓ.ም ላይ ከተቆጣጠሩ በኋላ በከተማዋ ድንጋጤ መፈጠሩን እና የሚያደርጉት ጠፍቶባቸው እንደነበር ታስታውሳለች ወጣቷ፡፡
ወንድሟን ጨምሮ ወንዶቹ በሙሉ ከተማዋን ለቀው ሲወጡ የሕወሃት ታጣቂዎች በየቤቱ እየዙሩ ሴቶችን ወንድሞቻችሁ፣ ባሎቻችሁ እና ልጆቻችሁ የት እንዳሉ ተናገሩ እያሉ ማስጨነቅ ይጀምራሉ፡፡
በወቅቱ የነበረውን ክስተት ቁጭት በቀላቀለ ተመስጦ ውስጥ ሆና የምታስታውሰው ሉባባ ስለሆነው እንዲህ ትናገራለች
“ኀሙስ ዕለት ነበር፡፡ መጀመሪያ አራት የጦር መሳሪያ የያዙ ወጣቶች ወደ ቤት መጡ ወንድምሽን አምጪ ካላመጣሽ እንደፍርሻለን አሉን፡፡ ወንድሜ የት እንዳለ አላውቅም ነበር ይሄንኑ ብነግራቸው አላመኑኝም፤ የያዙትን ክላሽ ወደ እኔ አዙረው እንገልሻለን አሉኝ ቆይቶ ደግሞ እንደፍርሻለን አሉኝ እንዲተውኝ ለመንኳቸው፡፡
የናንተ ወታደሮች የትግራይን ሴቶችን ለ10 ሲደፍሩ ነበር፡፡ እኛም እንደፍርሻለን አሉኝ ወዲያው አንደኛው በእርግጫ መታኝ፡፡ ስወድቅ አራቱም እየተፈራረቁ ደፈሩኝ፡፡”
ልጃገረድነቷን ጠብቃ ከእጮኛዋ ኒካህ የምታስርበትን ቀን ስትጠባበቅ የነበረችው ሉባባ በደረሰባት አሰቃቂ ጾታዊ ጥቃት ራሷን ስታ የሚሆነውንና የተደረገባትን በማስታውስበት አዕምሯዊ ይዞታ ውስጥ ነበረች፡፡ በጥቃቱ የዛለ ሰውነቷን ለማንቀሳቀስም የሚሆን የሆነውን ለማስታወስ አቅምም አልነበራትም፡፡ ራሷን ስታ በህይወትና በሞት መካከልም ነበረች፡፡ በበቀል የተነሳሱት አስገድዶ ደፋሪዎቿ እንደተንጋለለች ጥለዋት ሲሄዱ እንኳን አታስታውስም፡፡
ደም እየፈሰሳት ብቻዋን ባዶ ቤት ያለረዳት ሁለት የስቃይ ቀናትን ማሳለፏን የምታስታውሰው ሉባባ በጥቃቱ ማህጸኗ ቦታውን ለቆ ለከፍተኛ ስቃይ ከመዳረግም በላይ መራመድ አቅቷት እንደነበርም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግራለች፡፡
“ታጣቂዎች ባደረሱብኝ ጥቃት መቀመጥ፣ መራመድ፣ መተኛት እና መጸዳዳት አልችልም ነበር፡፡ ተስፋ ቆርጬ ህይወት አስጠልቶኝ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሆኖብኝ ነበር” ስትልም ነው የምትገልጸው፡፡
እስከ መሃል ሃገር ድረስ እስከ ሰሜን ሸዋ ለመዝለቅ ችሎ የነበረው የህወሓት ተዋጊ ኃይል ከጣርማበር ሊቀጥል ባለመቻሉ እየተመታ ወደመጣበት ለማፈግፈግ ለመሸሽም ተገዶ ነበር፡፡ በዚህም መርሳን ጨምሮ ሌሎች በህወሓት ቁጥጥር ስር የነበሩ አካባዎች ነጻ ወጥተዋል፡፡
ለከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃት ተዳርጋ እጅግ አስቸጋሪ የስቃይ ጊዜያትን ያሳለፈችው ሉባባም ከ4 ወራት በኋላ ህክምና አግኝታለች፡፡ እየሩስ አድማሴ በተባለች በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪነት በተደረገላት ድጋፍ ህክምና ማግኘቷን የምትናገረው ሉባባ አሁን በአንጻራዊነት የጤና ሁኔታዬ መሻሻል አሳይቷል ብላለች፡፡
"ወልዲያ፣ ደሴ እና አዲስ አበባ በተደረገልኝ ህክምና እርግዝናን ጨምሮ ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ነጻ መሆኔ ተነግሮኛል"ም ነው ሉባባ ያለችው፡፡
ነገን ተስፋ አድርጋ ጉልት ስትነግድ የነበረችው ሉባባ በጉጉት ትጠብቀው የነበረው ትዳሯ ኒካህ ማሰሩም ቀርቷል፡፡ ሁኔታዎች ሲከፉና መኖር ሲከብዳትም ሊያጋጥማት የሚችለውን መጠቋቆም በመፍራትም ወደ ትውልድ ከተማዋ መርሳ ላለመመለስ ወስናለች፡፡ አካባቢውን ለቅቄ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ መኖርን መርጫለሁ ስትልም ነው ለአል ዐይን የተናገረችው፡፡
ሉባባ ይህን ሁሉ እጅግ አስከፊ ጉዳት እና የህይወት መመሰቃቀል ያደረሱባት የህወሓት ታጣቂዎች አሁንም በድጋሚ በትውልድ አከባቢዋ ወረራ ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ታስባለች፡፡ የደረሰባትን በማስታወስም ዳግም የከፋ ጉዳትን ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ከፍ ያለ ስጋት አላት፡፡
ሆኖም በዚህ ስጋት ውስጥ ሆናም ቢሆን ህይወቷ በዚህ ሁኔታ እንዲቀጥል እንደማትፈልግ የምትናገረው ወጣቷ ቀድሞ ስትሰራው የነበረውን የጉሊት ንግድ ስራ መቀጠል እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡ ለዚህም ሰዎች የቻሉትን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉላት ጠይቃለች፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ይህን ለመሰለ እጅግ አአስከፊ አደጋ የተጋለጡ ሴቶች ጥቂት አይደሉም፡፡ ተመሳሳይ ጉዳትን ያስተናገዱ በርካቶች በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙም ሪፖርት መደረጉ ይታወሳል፡፡
ልክ እንደሷ ሁሉ ተመሳሳይ የመደፈር አደጋ የደረሰባቸው ብዙ ሰዎችን እንደምታውቅና ብዙዎቹ ህክምና እንዳላገኙ የምትናገርም ሲሆን አንዳንዶቹ በደረሰባቸው ጥቃት አዝነውና አፍረው በቤታቸው ህመማቸውን ይዘው መደበቃቸውን አክላለች፡፡
በጤና ሚኒስቴር የሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ አቤል ሞሴ ለአል ዐይን እንዳሉት የሉባባን የትውልድ አካባቢ መርሳን ጨምሮ በተለያዩ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በርካታ ሴቶች መደፈርን ጨምሮ ለተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች ተጋልጠዋል፡፡ ድጋፍ እየተደረገላቸውም ይገኛል፡፡
ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መሆናቸውን የተናገሩት ተወካይ ዳይሬክተሩ በትግራይ ክልል ሀገር መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌ እስከለቀቀበት ድረስ ለጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎች በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ሲደረግ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ከዛ በኋላ በአማራ እና አፋር ክልሎች በተከሰቱ ጦርነቶች ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የስነ ልቦና እና ክሊኒካል አገልግሎቶች በመሰጠት ላይ እንደሆኑም አቶ አቤል ገልጸዋል፡፡
በጦርነቱ የተጎዱ የጤና መሰረተ ልማቶች በአፋጣኝ ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ፣ የስነ ልቦና እና ክሊኒካል አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችሉ የአንድ ማዕከላትን በማቋቋም ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛልም ብለዋ አቶ አቤል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ነገር ግን መኖሪያቸውን የቀየሩ ሊኖሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን የተናገሩት ተወካይ ዳይሬክተሩ ጥቃቱ ደርሶባቸው አገልግሎት ያላገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ዜጎች የፌደራል፣ የክልል እና ከዚያም በታች ያሉ ተቋማት አደረጃጀቶች ተቀናጅተው ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑንም ነው ተወካዩ የተናገሩት፡፡