የኮሪያ ጦርነት ካበቃ በኋላ የሰላም ስምምነት ላይ ያልደረሱት የሁለቱ ኮሪያዎች ዉጥረት አሳሳቢ ሆኗል
ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ያላትን ሁሉንም ኦፊሴላዊ የግንኙነት መስመሮች አቋርጣለሁ አለች
በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል ያለውን የግንኙነት መስመር ጨምሮ ሁሉንም የግንኙነት መስመሮች እንደምታቋርጥ ሰሜን ኮሪያ ገለጸች፡፡
“ጠላት” በማለት በገለጸቻት ደቡብ ኮሪያ ላይ በተከታታይ ከሚወሰዱ ርምጃዎች ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ሰሜን ኮሪያ አስታውቃለች፡፡
በሰሜን ኮሪያ የድንበር ከተማ ካዞንግ ወደሚገኘው የመገናኛ መሥሪያ ቤት የሚደረጉ ዕለታዊ ጥሪዎች ዛሬ ማክሰኞ ዕለት ይቋረጣሉ ተብሏል፡፡
ካለፈው ሳምንት ወዲህ የደቡብ ኮሪያ አክቲቪስቶች ፀረ-ፒዮንግያንግ በራሪ ጽሑፎችን በድንበር በኩል እየላኩ መሆኑን በመግለጽ ሰሜን ኮሪያ ድርጊቱን ብታወግዝም ነገር ግን የአክቲቪስቶቹ ዘመቻ እስካሁን በመቀጠሉ ርምጃውን መውሰዷን ነው ሀገሪቱ ያስታወቀችው፡፡
የሀገሪቱ መንግስት በደቡብ ኮሪያ ላይ የሚወሰዱ ርምጃዎችን የሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፎችን በመላ ሀገሪቱ እንዳስደረገም ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በ 2018 ለሶስት ጊዜያት ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ውጥረትን ለመቀነስ ጽህፈት ቤት አቋቁመው ነበር፡፡
ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ እንደ አውሮፓውያኑ በ 1953 የኮሪያ ጦርነት ሲያበቃ ምንም ዓይነት የሰላም ስምምነት ባለማድረጋቸው አሁንም ድረስ ጦርነት ዉስጥ እንዳሉ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እናም የአሁኑ ርምጃ ወትሮውንም እልባት ያላገኘውን የሁለቱ ኮሪያዎች አለመግባባት ከሰከነበት መልሶ ወደ ዉጥረት እንዳያስገባው ተሰግቷል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ርምጃውን የወሰደችው የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሲንጋፖር ያደረጉት ታሪካዊ ስብሰባ ሁለት ዓመት ሊሞላው 3 ቀናት ሲቀሩት ነው፡፡
ባለፈው ዓመት በሃኖይ ቬትናም ለሁለተኛ ጊዜ ትራምፕና ኪም ባደረጉት ስብሰባ መግባባት ላይ አለመድረሳቸውን ተከትሎ በሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሐ ግብር ላይ የሚደረጉ ድርድሮች ተቋርጠዋል፡፡
ድርድሩ ከተቋረጠ በኋላ በሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ የሚሳይል ሙከራዎች መደረጋቸው ከዋሽንግተን ይልቅ ሴኡልን የሚያስጨንቅ እና ስጋት የፈጠረባት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ባለፈው ወር ከወታደር ነጻ በሆነው የሁለቱ ኮሪያዎች አዋሳኝ አካባቢ በሰሜን ኮሪያ ጀማሪነት አነስተኛ የተኩስ ልውውጥም ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡