የኢትዮጵያ መንግስት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ አስታውቋል
የሱዳን ጦር ዋና አዛዥ እና የሉዓላዊው የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ዛሬ በአል ፋሽቃ ድንበር አካባቢ ጉብኝት ማድረጋቸው ተሰማ፡፡
አልቡርሃን ወደ ስፍራው ያቀኑት ካርቱም “የኢትዮጵያ ወታደር በአካባቢው ጥቃት ሰንዝሯል” የሚል ክስ ካቀረበች በኋላ መሆኑን የአል ዐይን ዜና ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ በአካባቢው በነበረው ውጊያ ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸውን የተለያዩ የዜና ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ወታደራዊ ምንጮች እንዳሉት አል-ቡርሃን እና ሌሎች የሱዳን ጦር ከፍተኛ አመራሮች በአል ፋሽቃ አልሶግራ የሚገኘውን የታጠቁ ሃይሎች ግንባርን እንደጎበኙ ነው የተነገረው፡፡ የሱዳን ጦር፤ ትናንትና በአልፋሽቃ ድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ ጦር እና በታጣቂዎች በተከፈተ ጥቃት በርካታ አባላቱን ማጣቱን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የሱዳን መንግስት፤ የኢትዮጵያ ጦር "አርሶ አደሮችን ለማስፈራራት፣ የመኸር ወቅትን ለማክሸፍ እና ወደ ሱዳን ግዛት ለመግባት ያለመ ጥቃት አድርሷል” የሚል ክስ ያቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ ይህ ክስ ትክክል እንዳልሆነ ገልጿል፡፡
አዲስ አበባ፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ላላት ግንኙነትና ትስስር ትልቅ ቦታ የምትሰጥ መሆኗን ያስታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በሱዳን በኩል ሰርገው ለመግባትና ጥፋት ለመፈጸም በሞከሩ “የሽብር ቡድኑ” አባላት ላይ የተወሰደውን እርምጃ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በተሳሳተ መንገድ ሲዘግቡት መመልከቱን ይፋ አድርጓል፡፡
መንግስት ሁኔታው አሁን ኢትዮጵያ የጀመረችው የህልውና ዘመቻና “የሽብር ቡድኑን” የማስወገድ እንቅስቃሴ አንድ አካል እንጂ ሌላ ገጽታ እንደሌለው ገልጿል፡፡ “የሱዳን ወታደሮች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል” በሚል የወጡት ዘገባዎችም “ፍፁም” ሃሰት መሆናቸውንም የኢትዮጵያ መንግስት ትናንትና ባወጣው መግለጫ አብራርቷል፡፡
ኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻውን ማካሄድ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ ከሱዳን በኩል ሰርገው የሚገቡ ” የሽብር ቡድኑ የጥፋት ሃይሎች ጥቃት ለማድረግ ሲሞክሩ ቆይተዋል” ያለው የኢትዮጵያ መንግስትይህንንም ጥቃት ለመመከትና “የሽብር ቡድኑን እኩይ” እንቅስቃሴ ለማስቆም እርምጃዎች ተወስደዋል ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ላላት ግንኙነትና ትስስር ትልቅ ቦታ የምትሰጥ ሀገር በመሆኗ ፤ በሱዳን “ተወሮ” የሚገኘውን መሬት ጉዳይ በተመለከተ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገራቱን የዘመናት የታሪክና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ከግምት ያስገባ መፍትሄ ለማፈላለግ ጥረት እያደረገ እንደሆነም ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡