በአዲሱ የውጭ ምንዛሬ ተመን በንግድ ባንክ 1 ዶላር በ74 ብር እየተገዛ በ76 እየተሸጠ ይገኛል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች
ማሻሻያውን ተከትሎ በምንዛሬ ተመን በአንድ ዶላር ላይ በአማካይ የ18 ብር ጭማሪ ታይቷል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በዲሱን የምንዛሬ ተመን ዛሬ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ማሻሻውን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት መሸጋገሩን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ባወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን መሰረት አንድ የአሜሪካ ዶላር በ74.7364 ብር እየተገዛ በ76.2311 እየተሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊነትን ተከትሎ በምንዛሬ ተመን በአንድ ዶላር ላይ በአማካይ የ18 ብር ጭማሪ ታይቷል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምንዛሬ ዋጋ አንድ ፓውንድ ሰተርሊንግ 91.8787 ብር እየተገዛ በ93.7263 ብር እየተሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
እንዲሁም አንድ ዩሮ 81.0367 ብር እየተገዛ በ82.6574 ብር እየተሸጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግገድ ባንክ ዛሬ ባወጣው ዝርዝር የዋጋ ዝርዝር አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ በዛሬው እለት ጠዋት በሰጠው መግለጫ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ስለገለጸው በገበያ ወይም በፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ስለሚመሰረተው የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ነገሮች ይፋ አድርጓል።
ባንኩ እንደገለጸው የውጭ ምንዛሬ ተመን በባንኮች እና በደንበኞች መካከል እንዲወሰን ማድረግ፣ የውጭ ምንዛሬ ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስተላለፍ እንዲቀር፣ በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ገደብ እንዲነሳ፣ ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ለራሳቸው የሚያስቀሩት የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከ40-50 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም ባንኮች ለተለያዩ ሸቀጦች የሚጠቀሙበት የውጭ ምንዛሬ አሰራር እና አደላደል እንዲቀር እንደሚደግ፣ የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች እንደሚቋቋሙ፣ ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ከማስገባት ጋር በተያያዘ የተጣሉ ክልከላዎች በቅርቡ እንደሚሻሻሉ፣ በሀዋላ ወይም በውጭ ምንዛሬ የሚከፈል ደሞዝ ያላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የውጭ ምንዛሬ አካውንቲ እንዲከፍቱ መፈቀዱን እና የግል ኩባንያዎች ወይም ባንኮች በሚወስዷቸው የውጭ ብድሮች ላይ ይከፍሉት የነበረው የወለድ ተመን ጣሪ እንዲነሳ መደረጉን ብሔራዊ ባንኩ ጠቅሷል።