መንግስት የአገልግሎት ዘርፉ ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ከማድረጉ በፊት የሚሰበስበውን ታክስ በአግባቡ መጠቀም ላይ ሊያተኩር ይገባል - ምሁራን
ከአይ.ኤም.ኤፍ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ እስከ 500 የታሪፍ ጭማሪ ተደርጓል
አል ዐይን አማረኛ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ የሚደረጉ የአገልግሎት ታሪፍ ጭማሪዎች ህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል
ባሳለፍነው አመት ሀምሌ ወር ላይ መንግስት ከአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ ጋር ያደረገውን ስምምነት ተከትሎ የተለያዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው።
ከነዚህ መካከል የወለድ ምጣኔን ማስተካከል እና የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን መፍቀድ የሚሉት በምጣኔ ሀብቱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያላቸው ውሳኔዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ከባንኩ ጋር በተገባው ስምምነት መሰረት ገበያው ነጻ እነዲሆን፣ የሚደጎሙ ዘርፎች ድጎማቸው እንዲነሳ፣ የመንግስትን ወጪ በመቀነስ ገቢው ከፍ እንዲል ለማድረግ ተስማምተዋል።
በዚህም መሰረት በኢኮኖሚክስ መርህ የመንግስት ገቢ የሚያደግ ከሆነ አልያም ለድጎማ የሚያወጣው ወጪ የሚቀንስ ከሆነ የበጀት ጉድለትን ለመቀነስ የእዳ ጫናን ለማቃለል እንደሚያግዘው ይታመናል።
አዲስ የተሾሙት የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀስላሴ በሁለቱ ምክር ቤቶች ሰራ ማስጀመርያ የ2017 የመንግስት እቅድን ሲያቀርቡ “ከታክስ እና ታክስ ያልሆኑ ገቢዎችን በማሻሻል 1.5 ትሪሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን” ተናግረዋል።
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት እና በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢሜግሬሽን እና ፓስፖርት አገልግሎት፣ ጉምሩክ፣ ኤሌክትሪክ ፣ ባንኮች፣ የተሸከርካሪ ፈቃድ እና ሌሎችም አገልግሎቶች ከፍተኛ የዋጋ ማሻሻያ እንዲሁም የታክስ አገልግሎት ገቢራዊ አድርገዋል።
የሀገሪቱ መንግስት እያደረጋቸው የሚገኙ የአገልግሎት የታሪፍ ማሻሻያዎች አሁን ካለው የማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ አቅም እና የኑሮ ውድነት ጋር የሚሄድ አይደለም ሲሉ ብዙዎች ይደመጣሉ።
ሌሎች ደግሞ መንግስት ከአይኤምኤፍ ጋር ባለው ስምምነት መሰረት ድጎማን የማንሳት ግዴታ ስለተጣለበት አሰራሩ የሚጠበቅ ቢሆንም ገቢራዊ እየሆነ ያለበት ፍጥነት ነባራዊ ሁኔታዎችን አላገናዘበም ይላሉ።
አል ዐይን አማረኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ከምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
ዶክተር አለማየሁ ከበደ የናሽናል ፋይናስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት እና የገንዘብ ፖሊሰ ባለሙያ ናቸው፤ እሳቸው እንደሚሉ የምንዛሪ ጭማሪው በገበያ ውስጥ እንደሚፈጥረው የዋጋ ንረት ሁሉ መንግስትም በሚሰጠው አገልግሎት በገበያ ላይ የሚታየውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉ ተጠባቂ ነው።ይህም የምንዛሬ መጨመርን ተከትሎ የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ።
ባለሙያው “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በድጎማ የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ ነው በርካታ ዘርፎች ላይ መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር በግዢ በሚያቀርባቸው ምርቶች ላይ በጀት በመመደብ ድጎማ ሲያርግ ቆይቷል፤ አሁን የተፈራረመው ስምምነት ደግሞ እሱን እንዲያደርግ የሚፈቅድለት አይደለም ስለዚህ ድጎማ ሲያነሳም የታሪፍ ማሻሻያ ሲያደርግም ማህበረሰቡ ላይ ጫና መፍጠሩ አይቀርም” ባይ ናቸው።
መንግስት ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በገባው ስምምነት መሰረት የሀገር ውስጥ ገቢ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት እድገት አንድ በመቶ እና ከዛ በላይ እንዲሆን ይጠበቃል።
ከዚህ ባለፈም የፋይናንስ ፖሊስን በማስተካከል የዋጋ ንረትን መከላከል ፣የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ፋይናሻል አቅም በማጠናከር በሂደትም ወደ ግሉ ዘርፍ በማዘዋወር የመንግስት ሚና እንዲቀንስ ማድረግ የሚሉት ሌሎች የስምምነቱ ተጠቃሽ ነጥቦች ናቸው።
አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ የአግልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ ያደረጉትን መስርያቤቶች ብናነሳ ፓስፖርት 2 ሺህ ብር የነበረው ወደ 5ሺህ የ150 በመቶ ጭማሪ ፣ ከተሸከርካሪ ፈቀድ ጋር በተያያዘ ያሉ አገልግሎቶች ላይ ከ75 በመቶ-500 በመቶ ድረስ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም በየሩብ አመቱ የሚሻሻል አዲስ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ታሪፍ አስተዋውቋል ፣ ነዳጅ እና ትራንስፖርት ላይ በተደጋጋሚ እየታዩ ያሉ የዋጋ ጭማሪዎችም ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በነዳጅ ላይ የሚደረገውን ድጎማ ቀስ በቀስ እንደሚያነሳ መንግስት ማሳወቁን ተከትሎ ባለፉት ሶስት አመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ ይገኛል።
ሰኔ2014 ዓ.ም. በሊትር 47.8 ብር የነበረው ቤንዚን እንዲሁም በሊትር 49 ብር የነበረው ናፍጣ አሁን ላይ የቤንዚን ዋጋ በሊትር ወደ 91 ብር፣ ናፍጣ ደግሞ በሊትር ወደ 90 ብር ከፍ ብሏል።
ይህን ተከትሎም አዲስ በወጣው የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ በእጥፍ ዋጋ ጨምሯል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዋሲሁን በላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ማህበረሰቡ ከገበያው ሲጠበቅ የነበረው የዋጋ ጫና ከመንግስት እየመጣ ነው ይላሉ።
“ህብረተሰቡ ሲጠብቅ የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የሚፈጠረውን የኑሮ ተጽእኖ እንጂ የመንግስት የአገልግሎት ክፍያ ጨማሪውን አላሰበውም ፤ መንግስት ለምን ታሪፍ አሻሻለ ወይም ድጎማ ለምን አነሳ ብለህ መጠየቅ አትችልም እሱ የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያው አንድ ሂደት ነው፤ ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት ያደረጉት የታሪፍ ጭማሪ እጅግ የተጋነነ ነው ማሻሻያ መደረግ ካለበት የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተጠቀመው መንገድ ጥሩ የሚባል ነው በሂደት ቀስ በቀስ ፐርሰንቱን እያደገ መሄድ ሲገባው እስከ 500 ፐርሰንት ወጋ ጭማሪ መደረጉ ተገቢ ነው ብየ አላስብም” ነው ያሉት።
በነጻ ኢኮኖሚ ውስጥ ድጎማ ተግባራዊ እንዲደረግ የአይኤምኤፍ ፖሊሲ አይፈቅድም የሚሉት አቶ ዋሲሁን ይህን ከዚህ አንጻር መረዳት ከባድ ባይሆንም፤ መሰል ፈጣን ውሳኔዎች ገቢው ያልተሸሻለ ከእጅ ወዳፍ የሚባል ኑሮ በሚኖር ማህበረሰብ ውስጥ ማህበራዊ ቀውስን እንዳያስከትል ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።
አክለውም “የታሪፍ ጭማሪው አብዘሀኛውን ማህበረሰብ የሚነኩ መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ የተደረገ ነው ኤሌክትሪክ ፣ ውሀ እና ትራንስፖርትን ተወደደ ብለህ ልተዋቸው የምትችላቸው አገልግሎቶች አይደሉም ይህ ደግሞ የዜጎችን ወጪ ስለሚጨምረው የኑሮ ሁኔታውን ያባብሰዋል፤ ድጎማ ማንሳት ማለት ገበያውን መቆጣጠር አልያም ዋጋን ማረጋጋት የምትችልበትን አቅም ማጣት ማለት ነው ዋጋ ጭማሪው እየታየ ያለው ከፍተኛ የምርት አቅርቦት በሚስተዋልበት ገበያ ላይ መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን ያከፋዋል” ነው የሚሉት።
የሞኒተሪ ፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር አለማየሁ ከበደ የታሪፍ ማሻሻያዎች ከመደረጋቸው በፊት መንግስት የሚሰበስበውን ታክስ ምን ያህል በአግባቡ ይጠቀማል የሚለውን መፈተሽ እንደሚገባው ያሳስባሉ።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ለሙስና ተጋላጭ ተብለው ከተለዩ ዘርፎች መካከል የታክስ አሰባሰብ ፣ የመንግስት ግዢ እና የመሬት አስተዳደር ተጠቃሽ ናቸው፤ የታክስ ስርአት ካልዘመነ እና የተሰበሰበው ታክስ ደግሞ በአግባቡ መሰረታዊ የልማት ጉዳዮች ላይ የማይውል ከሆነ ገቢህ ቢጨምርም ካለህበት ወደ ፊት ለመጓዝ ይቸግራል” ሲሉ አብራርተዋል።
እንደ ዶክተር አለማየሁ ገልጻ መንግስት አሁን ባለው ሁኔታ ከግብር የሚያገኝው ገቢ ከደሀ ህዝብ የሚሰበሰብ እንደመሆኑ ምርታማነትን ሊያሳድጉ ፣ ግብርናን ሊያዘምኑ እና በአጠቃላይ ለኢኮኖሚው አቅም ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ እየተጠቀመበት እንደሚገኝ ሊፈትሽ ይገባል።
በተጨማሪም በቀጣይ መንግስት የታሪፍ ማሻሻያ ያደርግባቸዋል ተብሎ የሚጠበቁ ሌሎች አገልግሎቶች የሚፈጥሩንትን ማህበረሰባዊ የኑሮ ጫና ለመከላከል የተጠና እና በሂደት ሊከወን የሚችል ታሪፍን ተግባራዊ ለማድረግ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዋሲሁን በላይ ከዚህ በሚለየው ሀሳባቸው አሁን ጭማሪ ከተደረገባቸው አገልግሎቶች በፊት ከግብር ስርአት ውጪ ያሉትን ዘርፎች ወደ ስርአቱ በማስገባት ገቢን ማሳደግ የሚችልበት አማራጭ እንደነበረ ያነሳሉ።
ባለሙያው ከአይኤምኤፍ ጋር በተደረሰው ስምምነት በአራት አመት ውስጥ በሚኖረው አፈጻጸም ታይቶ ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ የሚለቀቅ መሆኑን ተከትሎ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡ እንዲፈጥን ተፈልጓል የሚል እምነት አላቸው።
በመፍትሄ ሀሳባቸውም መንግሰት ከገቢ ውጭ ያሉ ዘርፎችን ወደ ታክስ ስርአቱ ማስገባት ቢችል ፣ ከፕሮጀክት እና ከግዢ ጋር ተያይዞ የሚከተለውን የወጭ ስርአት ቢያስተካክል እንዲሁም ፣ የአምራቹን ክፍል አቅም ቢያጎለብት ኢኮኖሚያዊ ጫናውን መቋቋም እንደሚችል መክረዋል።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ድሕነት ግብርናው ነው የሚሉት ዶክተር አለማየሁ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የሸቀጦች እጥረትም ሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በጠንካራ ግብርና ሊቃለል እንደሚችል እና ዘርፉ ገና አለመነካቱን ይጠቁማሉ።
ቢያንስ በገበያ ውስጥ የሚታየውን የአቅርቦት እጥረት ማቀለል ቢቻል በቂ ምርት በተመጣጠነ ዋጋ የሚገበይ ማህበረሰብ ካለ በአገልግሎት ዘርፉ የሚመጣውን ጫና ለመቋቋም እንደሚያግዝም ነግረውናል።