ቫይረሱ ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ በሀገሪቱ የእንቅስቃሴ እገዳ እንዲጣል ባለሙያዎች እየጠየቁ ነው
በአሜሪካ ለ4 ተከታታይ ቀናት በየዕለቱ ከ1,000 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሞተዋል
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያሳየው በኮሮና ምክንያት የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ በሚገኝባት አሜሪካ በየዕለቱ ከ1,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ እየሞቱ ነው፡፡
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ እስከ ትናንት ድረስ በአሜሪካ ብቻ 146,460 ሰዎች በኮሮና ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸው ተገልጿል፡፡ ይሄን ተከትሎ በሀገሪቱ የእንቅስቃሴ እገዳ እንዲጣል ባለሙያዎች እየጠየቁ ነው፡፡
እርምጃ ካልተወሰደ እና የሟቾች ቁጥር አሁን ባለው ፍጥነት ከቀጠለ ከ20 ቀናት በኋላ በአሜሪካ በቫይረሱ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ 175,000 ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በተለይ ባለፉት 2 ሳምንታት በርካታ ግዛቶች ከቀድሞዎቹ ጊዜያት የላቀ የቫይረሱ ጠጠቂዎች እና ሟቾች ቁጥር መገኘቱን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ይሄም የሀገሪቱን ስጋት ያባባሰ ሲሆን አንዳንድ ግዛቶች ዳግም የእንቅስቃሴ እገዳ ሊጥሉ እንደሚችሉ እየገለጹ ነው፡፡
ባለፈው ሀሙስ እለት ከ150 በላይ የህክምና ባለሙያዎች ፣ ሳይንቲስቶች ፣ መምህራን ፣ ነርሶች እና ሌሎች ባለሙያዎች መሪዎች በመላው ሀገሪቱ የእንቅስቃሴ እገዳ ጥለው ቫይረሱን ለመቆጣጠር ለሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የሚጠይቅ ፊርማ አሰባስበዋል፡፡
ፊርማቸው ያረፈበትን ደብዳቤም ለትራምፕ አስተዳደር ፣ ለኮንግረስ አባላት እና ለየግዛቱ አስተዳዳሪዎች አስገብተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የትራምፕ መንግስት ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እየወተወተ ነው፡፡ የግዛት አስተዳዳሪዎች ት/ቤቶችን በቀጣዩ ወር እንዲከፍቱ ጫና በማሳደር ላይ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢገልጹም መምህራን ግን እርምጃውን እየተቃወሙ ነው፡፡
በተለይ በአንዳንድ ግዛቶች ቫይረሱ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ ት/ቤቶችን የመክፈት ሀሳብ ተቃውሞ እየገጠመው ነው፡፡
አንዳንድ ሆስፒታሎች ታማሚዎችን ማስተናገድ እንደተሳናቸው ጭምር እየተገለጸ ነው፡፡ ለአብነትም በቫይረሱ ሟቾች ቁጥር ባለፈው ሳምንት ክብረወሰን በያዘችው ቴክሳስ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ፣ ታማሚዎች ከቁጥጥር ዉጭ በመሆናቸው ፣ ዶክተሮች የቫይረሱ ታማሚዎች በወዳጆቻቸው ጥበቃ ስር ሆነው ሞታቸውን እንዲጠባበቁ ወደቤታቸው እየላኳቸው እንደሆነ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ማህበረሰባችንይህ ሊሆንበት አይገባውም ነበር ያሉት አንድ የቴክሳስ ባለስልጣን ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና ራሱን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡
በአሜሪካ እስካሁን ከ 4 ሚሊዮን 300 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ እስከ ትናንት ድረስ 146,460 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በመላው ዓለም ደግሞ ከ16 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 649 ሺ ያህል ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡