ፕሬዝዳንቱ እወስዳለሁ ያሉት መድሃኒት ለኮሮና ህክምና እንደማይውል እና ጉዳት እንዳለው ሀኪሞች ተናግረዋል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወባ መድሃኒት እየወሰዱ እንደሆነ ገለጹ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃይድሮክሲክሎሮክዊን እየተጠቀሙ እንደመሚገኙ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የወባ መድሃኒት የሆነው ሃይድሮክሲክሎሮክዊን ለኮሮና ቫይረስ ምንም ጠቀሜታ እንደሌለው ኤክስፐርቶች ቢገልጹም፣ ፕሬዝዳንቱ መድሃኒቱን እንደሚጠቀሙ መግለጻቸው አወዛጋቢ ሆኗል፡፡
ትራምፕ መድሃኒቱን እንደሚወስዱ የገለጹት ከሆቴሎች ስራ አስኪያጆች ጋር ዉይይት ባደረጉበት ወቅት ከሪፖርተሮች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ነጻ መሆናቸውን እና ምንም ምልክት እንደሌለባቸው የገለጹት ፕሬዝዳንት ትራምፕ መድሃኒቱን ግን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
“ላለፈው አንድ ሳምንት ከግማሽ በቀን አንድ ፍሬ በመውሰድ ላይ እገኛለሁ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋ፡፡ መድሃኒቱን ከመውሰዳቸው በፊት አንድ የኋይት ሀውስ ሀኪም ማመከራቸውን እና ሀኪሙም ከፈለጉ መውሰድ እንደሚችሉ እንደነገራቸው አብራርተዋል፡፡
የቤተመንግስቱ ሀኪም ሲን ኮንሌይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኮቪድ-19 ምርመራ በተከታታይ አድርገው ቫይረሱ እንዳልተገኘባቸው እና በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ “ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተደጋጋሚ ዉይይት ካደረግን በኋላ ሃይድሮክሲክሎሮክዊን መጠቀም ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚያመዝን ተስማምተናል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ሲጂቲኤን እንደዘገበው የአሜሪካ ምግብና መድሃኒት አስተዳደር ግን “የመድሀኒቱ ፈዋሽነት ወይም ጠቀሜታ አልተረጋገጠም” ብሏል፡፡ እንዲያዉም አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም ከወር በፊት ባወጣው መግለጫ መድሃኒቱን በተጠቀሙ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ላይ የልብ ምት ችግር እንዳስከተለ ገልጿል፡፡
የፕሬዝዳንቱን መግለጫ ተከትሎ አንዳንድ ሀኪሞች እና ድርጅቶች የኮቪድ-19 ታማሚዎች ሃይድሮክሲክሎሮክዊን እንዳይጠቀሙ በመምከር ላይ ናቸው፡፡ መድሃኒቱ ይህ ነው የሚባል ዉጤት የሌለው ከመሆኑም ባለፈ ከፍተኛ የልብ ህመም ሊያስከትል እና የልብ ምትን እስከማቆም ሊያደርስ እንደሚችል ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
በተቃራኒው የቫይረሱ ታማሚዎች መድሃኒቱን እንዲጠቀሙ የሚመክሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ከዚህ ቀደምም በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ለማገገም ሃይድሮክሲክሎሮክዊን ሊወስድ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡
ሃይድሮክሲክሎሮክዊን የተለመደው የወባ መድሃኒት-ክሎሮክዊን በልምምድ ብዛት ዉጤታማ በማይሆንባቸው አካባቢዎች አገልግሎት ላይ የሚዉል የተሻሻለ የወባ መድሃኒት ነው፡፡