በአሜሪካ ከተቃውሞ ሰልፍ ጋር ተያይዞ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው
በካሊፎርኒያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአማካይ በ46 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
ባለፉት ጥቂት ቀናት በሀገሪቱ 22 ግዛቶች የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል
በአሜሪካ ከተቃውሞ ሰልፍ ጋር ተያይዞ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው
በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚ ደረጃ ላይ በምትገኘው አሜሪካ ከጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ማድረጉን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በተለይ 22 ግዛቶች ላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በፍጥነት ማሻቀቡን ነው ዘገባው የሚያመለክተው፡፡ ግዛቶቹ የእንቅስቃሴ እገዳ ካላስቀመጡ የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ ተብሏል፡፡
የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከጨመረባቸው ግዛቶች አንዷ ፍሎሪዳ ናት፡፡ በግዛቲቱ ባለፈው አንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ በየዕለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአማካይ በ46 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡
በየትኛውም የዓለም ክፍል ቫይረሱ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን ዓለም አቀፍ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ትናንት በሰጡት መግለጫ ፣ ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ ከፍተኛው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው እሁድ ግንቦት 30 መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ በእለቱ “ከ136,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት ተደርጓል” ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ “ከነዚህም 75 በመቶ ያህሉ ከ10 ሀገራት ሪፖርት የተደረጉ ናቸው” ብለዋል፡፡
በሚያዝያ ወር የተወሰዱ ፣ ትምህርት ቤቶችን የመዝጋት እና በቤት የመቆየት ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ርምጃዎች በአሜሪካ ብቻ በቫይረሱ ሊጠቁ ይችሉ የነበሩ 60 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን መታደጉን የካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካ ዘረኝነትን እና የፖሊስ ርምጃን በመቃወም እየተካሄዱ ያሉ ሰላማዊ ሰልፎች ደግሞ አሁን ቫይረሱን ይበልጥ ሊያስፋፋው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ ቫይረሱ የሚተላለፍባቸው መንገዶች ደግሞ ብዙ መሆናቸው በሰልፈኞቹ አማካኝነት ስርጭቱ እንዲባባስ ምክንያት ይሆናል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ የበሽታዎች መከላከል እና ቁጥጥር ማዕከል በሀገሪቱ የሚካሄዱ ሰልፎችን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በባህር ዳርቻዎች የሚገኙ የአሜሪካ ግዛቶች ቀድመው በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቁ ሲሆን አሁን ደግሞ ስርጭቱ እንደ ቴክሳስ ፣ አሪዞና እና አርካንሳስ ያሉ ማእከላዊ ግዛቶች እየከፋ መጥቷል፡፡
በአሜሪካ እስካሁን ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከነዘህም ከ113 ሺ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡