የትራምፕ አስተዳደር ያዘጋጀው ባለ 5 ገጽ ረቂቅ ስምምነት ደብዳቤ ከዶ/ር ቴድሮስ እጅ ደርሷል
አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅትን በከፊል መደገፍ ልትደግፍ ነው
ለዓለም የጤና ድርጅት ታደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ያቋረጠችው አሜሪካ በከፊል ድጋፍ ለማድረግ መስማማቷ ተሰምቷል፡፡
በፎክስ ኒውስ ’ታከር ካርልሰን ናይት ሾው‘የተገኘውና ለድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የተላከ ነው የተባለለት ባለ 5 ገጽ ረቂቅ የስምምነት ወረቀት የትራምፕ አስተዳደር ልክ ቻይና እንደምታደርገው ሁሉ የአባልነት ክፍያውን ለመክፈል መስማማቱን ይገልጻል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሃገራቸው ታደርግ የነበረው ድጋፍ ለሁለት ወራት እንዲቋረጥ ማዘዛቸውን ያስታወቁት ከአንድ ወር በፊት ነበረ፡፡
በዚህም ከየአቅጣጫው ዘርፈ ብዙ ትችቶችን አስተናግደዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምም ቢሆኑ በወቅቱ የትራምፕን እርምጃ ተችተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ድርጅቱ እንዴት ነው ክፍያዎችን የሚያገኘው?
የአባልነት ክፍያው በሃገራት የእድገት ደረጃ እና በህዝብ ቁጥር ብዛት የሚከፈል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የድርጅቱ 194 አባል ሃገራት እና ሙሉ አባልነት የሌላቸው ሁለት ተባባሪዎቹ በየአመቱ ጥር አንድ በመጣ ቁጥር ይህንኑ ክፍያ ይከፍላሉ፡፡ እያንዳንዱ አባል ሃገርም 2 መቶ ሺ ዶላር እና ከዚያ በላይ የአባልነት ክፍያን በየአመቱ ይከፍላል፡፡
ድርጅቱ በሁለት አመታት የበጀት ዙር (ሳይክል) ነው የሚተዳደረው፡፡ ለተያዘውና ለቀጣዩ ፈረንጆቹ ዓመት (2020 እና 2021) ለእያንዳንዱ ዓመት 2 ነጥብ 4 ቢሊዬን ዶላር በድምሩ 4 ነጥብ 8 ቢሊዬን ዶላር በጀት እንደያዘም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ለድንገተኛ ብሎ የሚመድባቸውም ይኖራሉ፡፡
ይህ ከአባልነት ክፍያ እና በእርጥባን ድጋፍ የሚሸፈን ነው፡፡ ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዬን ዶላር በጀት ውስጥ 957 ሚሊዬኑ ከአባላት 4 ነጥብ 9 ቢሊዬን ዶላሩ ደግሞ ከእርጥባን የሚሰበሰብ ነው፡፡
በዚህ በጀት ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ የአሜሪካ ነው፡፡ በባለፉት ሁለት አመታት (እ.ኤ.አ 2018 እና 2019) ብቻ አሜሪካ ከድርጅቱ በጀት 20 በመቶውን ሸፍናለች፡፡ የተለያዩ ፕሮጄክቶችንም ትደግፋለች፡፡
የአሜሪካ ከፊል ክፍያ ምን ያህል ነው?
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሃገራው ለድርጅቱ ምታደርገውን ድጋፍ እንደምታቋርጥ ባስታወቁበት ወቅት በየዓመቱ ከ4 መቶ እስከ 5 መቶ ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸው ነበር፡፡በአባልነት ብቻ የምትከፍለው ክፍያም ድርጅቱ ከሚያገኘው አጠቃላይ የአባልነት ክፍያ ከ20 እስከ 22 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ መረጃ ያሳያሉ፡፡
ለምሳሌ በባለፈው በጀት ዓመት (2019) 119 ሚሊዬን ዶላር ከፍላለች፡፡ በተለያዩ ፕሮጄክቶች በኩል ደግሞ 300 ሚሊን ዶላርን አበርክታለች፡፡ ይህ አጠቃላይ በአመቱ ውስጥ ለድርጅቱ ፈሰስ ያደረገችውን የገንዘብ መጠን 420 ሚሊዬን ዶላር ገደማ ያደርሰዋል፡፡
አሜሪካ እንዳለችው ከቻይና እኩል ፈሰስ የምታደርግ ከሆነ ግን ከዚህ ቀደም ሲል ከተጠቀሰው 420 ሚሊዬን ዶላር ገንዘብ በአስር እጅ ያነሰ ወይም አንድ አስረኛውን ያህል ነው የሚሆነው፡፡
ቻይና ሁለተኛዋ የድርጅቱ ከፍተኛ የገንዘብ ደጋፊ ናት፡፡57 ነጥብ 4 ሚሊዬን ዶላርም በየአመቱ ፈሰስ ታደርጋለች፡፡ ጃፓን በየዓመቱ 41 ሚሊዬን ዶላር ፈሰስ በማድረግ ከግዙፍ የድርጅቱ የገንዘብ ደጋፊዎች ተርታ ተሰልፋለች፡፡
እንደ ፎክስ ኒውስ ከሆነ ቻይና የምትጨምር ከሆነ ሊጨምር የሚችልበትን ሁኔታ አስተዳደሩ እንደሚያጤንም ረቂቅ ደብዳቤው ይገልጻል፡፡
ነገር ግን ድርጅቱም ሆነ ዋና ዳይሬክተሩ በውሳኔዎቻቸውም ሆነ በስብሰባዎቻቸው ገለልተኛ እንዲሆኑ ደብዳቤው ያሳስባል፡፡
ትራምፕ ድርጅቱ አፍቃረ ቻይና (ቻይና ሴንትሪክ)እንደሆነ በመጥቀስና የቤት ስራውን በወጉ እየተወጣ እንዳልሆነ በመውቀስ ድጋፉን እንደሚያቋርጡ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡