በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 14 አርሶ አደሮች መገደላቸውን የዐይን እማኖች ተናገሩ
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 14 አርሶ አደሮች መገደላቸውን የዐይን እማኖች ተናገሩ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ በትናንትናው እለት 14 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአል ዐይን ተናገሩ፡፡
ግድያዋ የተፈጠመው ከጉባ ማንኩሽ ከተማ 16 ኪሜ ርቀት ላይ ያቡሉ በምትባል ቀበሌ ላይ መሆኑን ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ የዐይን እማኝ ተናግሯል፡፡
ግድያውን ለማውገዝና መንግስት ለህዝቡ ጥበቃ እንዲያደርግ የሚጠይቅ ሰልፍም በጉባ ማንኩሽ ተካሂዷል፡፡
የሟቾች አስከሬን ወደ አማራክልል ሰከላ መላኩን የዐይን እማኙ ጨምሮ ገልጿል፡፡
ግድያው የተፈጸመው ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎችና ቀስተኞች መሆኑን በአካባቢ ነበሩ የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች በእርሻ ስራ የተሰማሩ የአማራ ክልል ተወላጆች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
የዐይን እማኞቹ 14 ሰዎች መገደላቸውን ቢናገሩም የአማራ ክልል መንግስት ግን 11 ሰዎቸ መገደላቸውን ማረጋገጡን ለዐል አይን ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ 11 ሰዎች ሞታቸውንና ሌሎች መጎዳታቸውን ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
ግድያውን የፈጸሙት የለውጡ ተጻራሪዎች ያሰለጠናቸው ሰዎች ናቸው ያሉት አቶ ግዛቸው በጫካ ውስጥ ሆነው የሚንቀሳቀሱ እና ለይተው የሚገድሉ ሽፍቶች መሆናቸውንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት፡፡ አቶ ግዛቸው አሁን ላይ የቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው ተሰማርተዋል ብለዋል፡፡
የዚህ ግዲያ ዓላማ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት የታቀደ እንደሆነ የገለጹት አቶ ግዛቸው በቅርቡ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ባደረጉት ጥረት ከዚህ በፊት ተፈናቅለው የነበሩት ሰዎች እንድመለሱ መደረጉን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት በኢትዮጵያ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰፍረው ቆይተው ነበር፡፡ የክልሉ መንግስት ባለፈው ግንቦት ወር አብዛኞቹን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሱን አስታውቆ ነበር፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ በኩል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ክልሉ ፖሊስ ኮሚሺን ደውለን ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡