በአንዴ 92 ናሙናዎችን የሚመረምረው ማሽን በአንድ ቀን እስከ 300 ተጠርጣሪዎችን ሊመረምርም እንደሚችል ተገልጿል
በቤንሻንጉል ኮሮናን መመርመር ተጀመረ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስን መመርመር ተጀምሯል፡፡ ምርመራው የተጀመረው የክልሉ መንግስት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት እና ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ባገኘው ፒ.ሲ.አር የምርመራ ማሽን ነው፡፡
ማሽኑ በአንዴ 92 ሰው የመመርመር አቅም አለው፡፡ በቀን በአማካይ እስከ 300 ተጠርጣሪዎችን ሊመረምርም ይችላል። ትናንት በመከራ ደረጃ 9 ሰዎችን መርምሮ ውጤታማ ስለመሆኑም ተረጋግጧል፡፡
ቀደም ሲል ማሽኑ ባለመኖሩ 360 የሚሆኑ የክልሉ ተጠርጣሪዎች ናሙና ወደ አዲስ አበባና ባህር ዳር ተልኳል ያሉት የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬህወት አበበ ማሽኑ ይህን ያስቀራል ብለዋል፡፡
የክልሉን የመመርመር አቅም ከማሳደግም በላይ ቤት ለቤት በአሰሳ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች እንዲሁም በለይቶ ማቆያ የሚገኙትን በተፈለገው ጊዜ ለመመርመር እንደሚያስችል እና ለአጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች እንደሚጠቅምም የተናገሩት።
ማሽኑ ባለመኖሩ ምክንያት ወረርሽኙን የመከላከሉ ስራ አዳጋች ሆኖ ነበር ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ተጠርጣሪዎችን በስፋትና በቶሎ ለመመርመር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የመመርመሪያ ክልላዊ ላብራቶሪውን በቀጣይ ወደ ምርምር ኢኒስቲትዩት ለማሳደግ ይሰራልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።