ኢዜማ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) የታጠቁ ኃይሎችን በመደገፍ ሳይጠረጠሩ እንዳልቀሩ ፍንጭ ሰጥቷል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው መግለጫ መስከረም 13 የታሰሩበት ሊቀመንበሩ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) እስራቸው "በፓርቲው ባላቸው ኃላፊነት" ምክንያት አይደለም ብሏል።
ፓርቲው የሊቀመንበሩን እስር እንዲከታተል ሰየምኩት ያለው ኮሚቴ አደረገው ባለው ማጣራት፤ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር )በቁጥጥር ስር የዋሉት "በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ተጠርጥረው" ነው ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።
ኢዜማ ባለፈው ሳምንት ሊቀመንበሩ የእስር ማዘዣ ሳይቀርብባቸው ታርጋ በሌለው ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር እንደዋሉበት ማስታወቁ ይታወሳል።
እስሩንም "ህግ እና ስርዓትን ያልተከተለ እርምጃ ነው" ሲልም በጽኑ እንደሚያወግዘው ገልጾ ነበር።
ኢዜማ የሊቀ-መንበሩን የእስር ሁኔታ በአንድ አንቀጽ ብቻ በገለጸበት መግለጫው፤ ከሰላማዊ የትግል ውጪ የብሄርተኝነትና የአፈ-ሙዝ ትግል የቆምኩበትን መርህ ይቃረናል ብሏል።
ከዚህ አቋም ውጭ የሚንቀሳቀስ የኢዜማ አባልና አመራር ድርጅቱን ለማፍረስ እንደሚሰራ ተደርጎ ይቆጠራል ሲል ሊቀ-መንበሩ ተሳትፎ ግልጽ ሳያደርግ አስታውቋል።
ሆኖም አማራ ክልል ላይ ባለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጋር ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
ፓርቲው "ኢዜማ ውስጥ የማይነካም ሆነ የማይተካ አባልም ሆነ አመራር የለም" በማለትም አሰምሯል።
በመሆኑም ያለው ፓርቲው ከድርጅቱ ዓላማ እና የትግል መስመር ባፈነገጠ መንገድ በሚንቀሳቀሱ አባላቱ ላይ የጸና አቋም ይይዛል ብሏል።
ከሰላማዊ ትግልና ከዜግነት ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውጭ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መደገፍ፣ የሀሳብም ሆነ የተግባር ተሳትፎም ሆነ ትብብር ማድረግ ከመርሁ ማፈንገጥ መሆኑን ገልጿል።
የሊቀመንበሩን ጉዳይም ከዚህ መርህ አንጻር የሚታይ ነው ሲል በተዘዋዋሪ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) የታጠቁ ኃይሎችን በመደገፍ ስለመጠርጠራቸው አመላክቷል።