ልዩ ሀይሎች ወደ ፌደራል እና ክልል የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ግልጸኝነት እንዲፈጥር ኢዜማ አሳሰበ
ኢዜማ የክልል ልዩ ሀይሎችን ወደ "ህጋዊ የጸጥታ መዋቅር" የማስገባት ተግባር እንደሚደግፍ ገልጿል
መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን ወደ ፌደራል ወይም ወደ ክልል የጸጥታ እንዲካተቱ እንደሚፈልግ አስታውቋል
መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን ወደ ፌደራል ወይም ክልል የጸጥታ ተቋማት እንዲካቱ ከማድረጉ በፊት ግልጸኝነትን እንዲፈጥር ኢዜማ አሳሰበ፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራልና የክልል ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባት በጎ ጅምር ቢሆንም ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡
ፓርቲው እንዳለው ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ከሕጋዊ አሠራር ውጪ እንዲቋቋሙ የተደረጉ የክልል ልዩ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ዕዝ ሥር እንዲገቡ መደረጉ ተገቢም ልክም ነው ብሏል።
ፓርቲው የዘውግ ፖለቲካ ነፀብራቅ የኾኑ የክልል ልዩ ኃይሎች እየፈጠሩ ከነበረው ሀገራዊ አደጋ አንፃር ከስመው ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲገቡ ከዚህ በፊህ አቋሙን በተለያዩ ሁኔታዎች እና መድረኮች ላይ ሲያሳውቅ እንደነበርም አስታውሷል።
በአስተዳደር ወሰን ይገባናል ጥያቄ መነሻ የኦሮሚያ ፣ የሶማሌ፣ የአማራ፣ የሲዳማ፣ የአፋር እና የቤንሻንጉል ልዩ ኃይሎች አንዳቸው ከሌላኛው ጋር መጋጨታቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው ያለው ኢዜማ " ይህ ሁኔታ አሁንም ድረስ በአንዳንድ ክልሎች መካከል መቀጠሉ ንፁሀን ዜጎችን ከመጉዳቱም ባሻገር የሀገር ሉዓላዊነት ላይ አደጋ መደቀኑን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም፤ ከሕግ አግባብ ውጪ በአንድ ክልል ወይም ዘውግ ጠባቂነት የተቋቋሙ የክልል ልዩ ኃይሎች ከስመው በህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ሥር መጠቃለላቸውን የምንደግፈው ተገቢ ውሳኔ ነው ሲል አቋሙን ገልጿል።
ይሁንና የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ሥር መግባታቸውን ከልቡ የሚደግፈው ውሳኔ ቢሆንም አተገባበሩ ፈንጅ የማምከን ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ ኢዜማ በመግለጫው አሳስቧል፡፡
ለአብነት በቅርቡ ከአሸባሪነት መዝገብ እንዲፋቅ የተደረገው የህወሓት ቡድን በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን በኩል በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ሥር ያሉ አካባቢዎችን ስለማስመለስ እንደሚሠራ በስፋት እያስተጋባ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ይህንን ውሳኔ በጥድፊያ እና በድብቅ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አደገኛ ውጤት እንደሚያመጣ የፌደራል መንግሥት ሊገነዘበው ይገባልም ብሏል።
ህወሓት የታጠቃቸውን መሣሪያዎች መፍታቱ በግልጽ ባልታወቀበት ሁኔታ የትግራይ አዋሳኝ ክልሎች ዳግም የመወረር ስጋት ቢያድረባቸው የሚያስወቅስ አይደለም ያለው ኢዜማ የውሳኔውን አፈጻጸም ቅደም ተከተል በተመለከተ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አስገንዝቧል።
በመሆኑም የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን ተጥቅ ለማስፈታት እየሄደበት ያለው መንገድ ግልጸኝነት የጎደለው በመሆኑ አሰራሩ በግልጽ መግባባት ውይይት ከተደረገበት በኋላ ሊደረግ እንደሚገባ ኢዜማ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የፌደራል መንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ የክልል ልዩ ሀይሎችን ወደ ፌደራል ወይም ወደ ክልል የጸጥታ መዋቅር የማካተት ስራ መጀመሩን ገልጾ ድርጊቱ በአማራ ክልል ብቻ የተጀመረ ነው በሚል የተሰራጨው መረጃ ትክክል አይደለም ብሏል፡፡
መንግስት የተማከለ ብሔራዊ የጸጥታ መዋቅር ለመገንባት መወሰኑን የገለጸው መግለጫው ሁሉንም የክልል ልዩ ሀይሎችን ተጥቅ እንደሚፈቱም አስታውቋል፡፡