የአቶ ግርማ የሽጥላ ግድያ "በገለልተኛ አካል" እንዲመረመር እና ፍረጃ እንዲቆም ኢዜማ ጠየቀ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንትነው እለት "ነውጠኛ እና ጽንፈኛ ኃይሎች" በአቶ ግርማ ላይ ግድያ መፈጸማቸውን መግለጻቸው ይታወሳል
በግድያው ሀዘኑንን የገለጸው ኢዜማ በግድያው ዙሪያ የሚደረግ ትንተናና ፍረጃ አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጿል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፖርቲ(ኢዜማ) የአማራ ብልጽግና ፖርቲ ኃላፊ የአቶ ግርማ የሽጥላ ግድያ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ጠይቋል።
መንግስት ለግድያው ጽንፈኛ ያላቸውን ኃይሎች ተጠያቂ አድርጓል።
በግድያው ሀዘኑን የገለጸው ኢዜማ በግድያው ዙሪያ የሚደረግ ትንተናና ፍረጃ አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጿል።
ኢዜማ ባወጣው መግለጫ "የመንግሥት ባለሥልጣናት ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በግድያው ዙሪያ ትንተና፣ ፍረጃ እና የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ከሚደረግ ሩጫ እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።" ብሏል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ ድርጊቱ አግባብ ባለው የህግ አካል መጣራት አለበት ብሏል።
አብን የግድያ ሁኔታው ሳይጣራ እና አጥቂዎቹ ሳይታወቁ ከግድያው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግን ፍረጃ እንደሚያወግዝ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንትነው እለት "ነውጠኛ እና ጽንፈኛ ኃይሎች" በአቶ ግርማ ላይ ግድያ መፈጸማቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
የአማራ ክልል መንግስትም ግድያውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች" ግድያውን መፈጸማቸውን እና በእነዚህ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
አቶ ግርማ የሽጥላ ጠባቂዎችም በጥቃቱ ተገድለዋል ተብሏል።
አቶ ግርማ የሽጥላ የአማራ ብልጽግና ኃላፊ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በአማራ ክልል በተለያዩ ኃላፊነቶች ሰርተዋል።