ኢዜማ ሊቀመንበሩ በምን ምክንያት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አላወኩም ብሏል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።
ሊቀመንበሩ እሁድ መስከረም 13፤ 2016 ዓ.ም. በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ፓርቲያቸው አስታውቋል።
ታርጋ በሌለው ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉት፤ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) የእስር ማዘዣ አልቀረበባቸውም ተብሏል።
ኢዜማ ሊቀመንበሩ በምን ምክንያት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አላወኩም ብሏል።
ህግ እና ስርዓትን ያልተከተለ እርምጃ ነው ሲልም ፓርቲው በጽኑ እንደሚያወግዘው አስታውቋል፡፡
ጉዳዩን በጥንቃቄ እና በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን የተናገረው ኢዜማ፤ በዚህም አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጉን ገልጿል።
የፓርቲው ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል ኮሚቴ ማቋቋሙን ተናግሯል።
በአማራ ክልል ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ መንግስት የምክርቤት አባላትን ጨምሮ በርካቶች ማሰሩ ይታወሳል።