የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ አባልን ያለመከሰስ መብት አነሳ
ምክርቤቱ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ዶክተር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ መብት ነው ያነሳው
የምክርቤቱ አባሉ ያለመከሰስ መብት የተነሳበት ዝርዝር ጉዳይ በፍትህ ሚኒስቴር ተጣርቶ ቀርቧል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባከሄደው 13ኛ መደበኛ ጉባኤው የብልጽግና ፓርቲ አባል የሆኑ የምክር ቤቱን አባል ያለመከሰስ መብት አንስቷል።
ምክርቤቱ የዶክተር ጫላ ዋታን ያለመከሰስ መብት ነው ያነሳው።
የፍትህ ሚኒስቴር የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ መብታቸውን ያስነሳሉ ያላቸውን ጉዳዮች በማጣራት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ልኳል።
ኮሚቴውም ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቶ ዛሬ የውሳኔ ሃሳቡን አቅርቦ ምክርቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን አንስቷል።
ዶክተር ጫላ ዋታ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት፥ የተለያዩ የማማከር ስራዎችን የሚያከናውን ድርጅት አቋቁመው ዩኒቨርሲቲውን ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸው ተገልጿል።
ዶክተር ጫላ ቢ ኤች ዩ ኮንሰልታንስ የተባለ ድርጅትን በማቋቋም በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መሳተፋቸውን የፍትህ ሚኒስቴር ባደረገው ማጣራት ማረጋገጡን ነው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የገለጹት።
ከ23 ሚሊየን ብር በላይ ከዩኒቨርሲቲው አካውንት ወደ ድርጅቱ ያለአግባብ ገቢ መደረጉን ያነሱት ሰብሳቢዋ፥
195 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የግንባታ ስራዎችን ለ9 ተቋራጮች ከመንግስት የግዥ አዋጅና መመሪያ ውጪ በቀጥታ እንዲፈጸም ማድረጋቸው መረጋገጡንም አብራርተዋል።
116 ሚሊየን ብር የሚያወጡና ዋጋቸው እጅግ የተጋነነ 14 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች በግል ተቋራጭ ድርጅት ስም ግዥ ተፈጽሟል የሚለውም በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተነስቷል።
ዩኒቨርሲቲው ለካፒታል ወጪ የተመደበለትን በጀት ያለአግባብ መጠቀማቸውን የኦዲት ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱም ነው የተጠቆመው።
በባለቤታቸው ስም 10 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ህንጻ ገዝተዋል የሚለውም የተነሳው ጉዳይ ነው።
ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ዶክተር ጫላ ዋታ በሰጡት ምላሽም ቢ ኤች ዩ ኮንሰልታንስ የዩኒቨርሲቲው የገቢ ማመንጫ ድርጅት ነው።
በድርጅቱ በኪል የሚፈጸሙ የገንዘብ ዝውውሮችም የዩኒቨርሲቲው ናቸው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አብዛኞቹ የተጠቀሱት ጉዳዮችም በዩኒቨርሲቲው የኦዲት ሪፖርቶች ላይ የተመላከቱ ናቸው በሚል አስተባብለዋል።
ይሁን እንጂ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚም ሆነ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጫላ ናቸው፤ ፈቃዱም በሳቸው መውጣቱን በምርመራ ስራው ተረጋግጧል ነው ያሉት።
የዶክተር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ መብት በአንድ ድምጸ ተአቅቦ (በራሳቸው በዶክተር ጫላ) በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።